ተተኪ መሪዎች ከቀድሞ ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ የተሻሉ መሪዎች መሆን ይገባቸዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ተተኪ መሪዎች ከቀድሞ ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ የተሻሉ መሪዎች መሆን ይገባቸዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአዲሱ ትውልድ ተተኪ መሪዎች ከቀድሞ ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ የተሻሉ መሪዎች መሆን ይገባቸዋል አሉ። በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚደረገው ሽግግር "በመመሰጋገንና በመተራረም ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል" ብለዋል። የአዲሱ ትውልድ ተተኪ መሪዎች ያለፈውን ትውልድ ከመውቀስ ይልቅ "ያለ ትላንት ዛሬ አልተገኘምና" ያለፈውን ትውልድ አመስግነው ማክበር ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል። "አገር የምታድገው በቅብብሎሽ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቀደመው ትውልድ ልምድና ጥበብ ለአዲሱ ትውልድ የመሪነቱን በትር ሊያስረክብ እንደሚገባም ጭምር ነው ያስገነዘቡት። የአዲሱ ትውልድ ተተኪ መሪዎች ከቀድሞ ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ የተሻሉ መሪዎች መሆን እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት የሰጡት ጠቅላዩ፤ እኛም በተራችን በሌላ ትውልድ ተተኪ መሆናችን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አንዱ የፖለቲካ ኪሳራ "መተካካት መበላላት መሆኑን" የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ "መተካከካት የታቀደ ሂደት ሆኖ እንዲመጣ እንጂ ድንገተኛ የመበላላት ክስተት እንዳይሆን ሥርዓት መትከል ያስፈልጋልም" ብለዋል። በኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚደረገው የስልጣን ሽግግር በመመሰጋገንና በመተራረም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርግ የፖለቲካ ባህል ለማስረጽ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል። "የአንድ መሪ ስኬታማነት የሚለካው እሱ የጀመረውን አስፍተው መቀጠል የሚችሉ አመራሮችን ምን ያህል አፍርቷል?" የሚለው በመሆኑይህንን ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ብለዋል። አዲሱ ትውልድ ስልጣን በእጁ አስገብቶ በተለመደው አገራዊ የስልጣን ጥማት ክፉ ባህል ቀድሞ የነበረውን ሁሉ በማፍረስ የሚጠመድ መሆን አንደማይገባው እና ትላንት በነበሩ በጎ እሴቶች ላይ ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ጋር ያጣጠመች አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ታጥቆ መነሳት አለበት ብለዋል። "የአዲሱ ትውልድ መሪዎች የምናስረክባትን ኢትዮጵያ አስውበን መቅረጽና ለተተኪው ማስረከብ የሁላችንም ግዴታ ነው" ሲሉም ተናግረዋል። በመጨረሻም ጉባኤው የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር፤ በሂደቱ የነበሩትን ጉድለቶችንና ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ተግዳሮቶች ነቅሶ በማውጣትም የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋገርበት ነውም ብለዋል።