አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ከአራት ዓመት በኋላ ዛሬ ወደ ውድድር ትመለሳለች

89

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 7/2015 ስኬታማዋ የረጅም ርቀት ሯጭ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ዛሬ በአሜሪካ በሚካሄደው የሂውስተን ግማሽ ማራቶን ወደ ውድድር ትመለሳለች።

የሶስት ጊዜ የኦሊምፒክ እና የአምስት ጊዜ የዓለም አትሌትቲክስ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ጥሩነሽ ባለፉት አራት ዓመታት ምንም አይነት ውድድር ላይ አልተሳተፈችም።

ዛሬ ለ22ኛ ጊዜ በሚካሄደው የሂውስተን ማራቶን ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ጥሩነሽ ዲባባ ትገኝበታለች።

አትሌት ጥሩነሽ በርቀቱ ያስመዘገበችው ፈጣን ሰአት እ.አ.አ በ2017 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተካሄደው የራስ አልካይማህ ግማሽ ማራቶን 1 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ነው።

በውድድሩ ላይ የጥሩነሽ ታናሽ እህት አና ዲባባም ትሳተፋለች።

አትሌት ሕይወት ገብረኪዳን እና አትሌት አፀደ ባይሳ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

አትሌት ሹራ ቂጣታ እና አትሌት ልዑል ገብረስላሴ በወንዶች ግማሽ ማራቶን ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።

በሌላ በኩል ዛሬ በስፔን ቫሌንሺያ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የጎዳና ላይ ውድድር የኬንያ እና ዩጋንዳ አትሌቶች የዓለምዘርፍ ዋነኛ ተፎካካሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም