ግምታዊ ዋጋቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን በጉጂ ዞን የአዶላ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ

129

ነገሌ (ኢዜአ) ጥር 6/2015 ዓ.ም በጉጂ ዞን አዶላ ወረዳ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብዱልከሪም ሁሴን እንደገለጹት እቃዎቹ የተያዙት ከጥር 3 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በአዶላ ወረዳ ቦኬ ቀበሌ በተደረገ ፍተሻ ነው፡፡

ከተያዙት እቃዎች ውስጥ ልዩ ልዩ መድሀኒቶች፣ 4 ኩንታል ጫማዎች፣ 20 ኩንታል ልባሽ ጨርቆች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

አጠቃላይ የኮንትሮባንድ እቃዎቹ አንድ ሚሊዮን 15 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዝውውሩን ለመግታት ከወረዳው ህዝብ ጋር በመተባበር አሁንም እየተደረገ ያለው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡

ፖሊስ በዚህ አመት ባደረገው የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር በህዝብ ጥቆማና በፍተሻ ነዳጅ፣ ልባሽ ጨርቆች፣ መድሀኒቶችንና ሌሎችንም እንደያዘ አስታውሰዋል፡፡

በህገ ወጥ መንገድ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችና መድሀኒቶች ከሚያስከትሉት የጤና ችግር ባለፈ ፍትሀዊ የንግድ ውድድርን ያዛባሉ ብለዋል፡፡

የዞኑ ሕዝብ ስልትና አቅጣጫውን እየቀየረ የመጣው የኮንትሮባንድ ዝውውር በመጠቆም የጀመረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም