በኦሮሚያ ክልል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ በትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 06/2015 በኦሮሚያ ክልል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል በወጪ ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ከባንክ የሥራ ኃላፊዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት ለወጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራትና በብዛት እንዲመረቱ በትኩረት እየሰራ ነው።
ከክልሉ ለወጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በገበያው ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በምርምር፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ታግዘው በመስኖ ልማት ጭምር በጥራት፣ በብዛትና በፍጥነት እንዲመረቱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም መንግሥት ዘርፉን ለማሳለጥ የጀመራቸው ስራዎች በበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በክልሉ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍና እገዛ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ የመንግሥት ሀብት አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ከክልሉ የግብርና፣ የማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ዘንድሮ ከክልሉ ለውጭ ገበያ ከሚቀረቡ ምርቶች 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለውጪ ገበያ የሚቀርብ በ6 ሺህ ሄክታር ላይ እየለማ ያለው የአቫካዶ ተክል ለዘርፉ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በስንዴ ምርትም የኦሮሚያ ክልል 15 ሚሊዮን ኩንታል ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንጻሩ ከክልሉ አሁንም ለውጪ ገቢያ እየቀረቡ ያሉት የቁም እንስሳት፣ የስጋ፣ የማርና የቅመማ ቅመም ምርቶች ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ እንደሆኑም ዶክተር ግርማ ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግሥት የውጭ ገበያ ተኮር ምርቶችን የሚያመርቱ አምራቾችም የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የወጪ ንግድ ለሀገር ካለው ጠቀሜታ አንጻር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ከምርት ጥራት ጋር በተያያዘ በተለይም የቡና ምርት ጥራት ችግር በዘርፉ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የሚጣለው ከፍተኛ ቀረጥ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መሰል ችግሮች የወጪ ንግዱን እየጎዱት እንደሆነ አስረድተዋል።
በተለይም በማዕድን ዘርፍ እየተበራከተ ያለው ህገ-ወጥ ንግድ ከዘርፉ ለውጪ ገበያ የሚቀርበው ምርት አነስተኛ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው፤ መንግሥት ችግሮቹን እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ከታክስ ጋር የሚያያዙ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚሰራ የገለጸ ሲሆን የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።