ዲፕሎማቶች የሃገራቸውን ምርቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ለኮኖሚያዊ እድገት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማቶች የሃገራቸውን ምርቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ለኮኖሚያዊ እድገት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 6/2015 ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እና ምርቶችን በማስተዋወቅ ለአገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
"የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና የግሉ ዘርፍ" የውይይት መድረክ በሚል መሪ ሃሳብ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፤በንግድ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ምክክር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ሚኒስትር ዲኤታው “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማምጣት አዳጋች ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ዲፕሎማቶች በተለይም ወደ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት እና ምርቶች “ተጨባጭ በሆነ መረጃ ላይ በመመስረት” ሊያስተዋውቁ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ለዚህም መንግስት ለዲፕሎማቶች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የሆነ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው መድረኩ ከአዳዲስና ነባር ዲፕሎማቶች ጋር የሀገሪቱን የንግድ ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር የንግድ ተስስር ኢንዲፈጥሩ በማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ ዲፕሎማቶች ሚናቸውን እንዲጫወቱ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።