የቅርሶችን ደህንነት ለመጠበቅ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራሁ ነው-የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የቅርሶችን ደህንነት ለመጠበቅ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራሁ ነው-የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን
ዲላ (ኢዜአ) ጥር 06/2015 በዓለም ሃብትነት የተመዘገቡ ቅርሶችን ደህንነት ለመጠበቅና አዳዲስ ቅርሶችን ለማስመዝገብ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
ዲላ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የሶስት ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉበት የቅርሶች ጥበቃ ላይ ያተኮረ የምርምር ፕሮጀክት በዲላ ከተማ ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ አዳዲስ ቅርሶችን ለማስመዝገብ በመሰራት ላይ ነው።
ከዚህ ቀደም የተመዘገቡት ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተለያዩ ምክንያቶች በቅርስ አጠባበቅና አስተዳደር የገጠማቸውን ጫና ለመፍታት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና የባሌ ተራሮችንና ብዝሃ ህይወት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ተግባራት በጋራ እየተከናወኑ መሆናቸውን ለዓብነት አንስተዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመንና ኬንያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የጀመሩትና የኮንሶ መልክዓ ምድርና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቅርስ ደህንነትና ጥበቃ ላይ ያተኮረው ይህ ፕሮጀክት የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ባለስልጣኑ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱን አስመልክተው ገለጻ ያቀረቡት ከጀርመን ቦን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ግርማ ቀልቦሬ የምርምር ፕሮጀክቱ በሀገራቱ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶች የተጋረጠባቸውን ጫና ተቋቁመውና ተጠብቀው እንዲቆዩ ማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በይበልጥ በኢትዮጵያ ለኮንሶ መልክዓ ምድርና በኬንያ የሚጂኬንዳ ካያ የጥብቅ ስፍራዎች ጥበቃ ላይ እንዳተኮረም ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ወጪ በቮልስዋገን ፋውንዴሽን የሚሸፈን ሲሆን ከጀርመን ቦን ዩኒቨርሲቲ፣ ከኬንያ የኬንያታ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በጥምረት የሚተገበር መሆኑንም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ለምርምርና ለምሁራን ስልጠና 70 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተመደበለት ሲሆን ለአራት ዓመታት እንደሚተገበርም ተመላክቷል።
በሰሜን ኬንያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙትን ዓለም አቀፍ ቅርሶች ደህንነታቻውን ማስጠባቅ በቀጠናው የቱሪስት ፍሰት እንዲጠናከር በማድረግ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ድርሻው የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሚሳተፍበትና በሶስቱ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የሚከናወነው የምርምር ፕሮጀክት ምሁራን የጥናት አቅማቸውንና ልምዶቻቸውን የሚጋሩበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኮንሶ መልክዓ ምድርና በኬንያ የሚጂኬንዳ ካያ የጥብቅ ስፍራዎች በፕሮጀክቱ በምርምር የተደገፈ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የመፍትሔ ሀሳቦች የሚቀርቡበትና ለፖሊሲ ግብአት የሚገኝበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከ18 በላይ የምርምር ፕሮጀክቶች በጋራና በተናጠል በመተግበር ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመድረኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከኮንሶ አካባቢ የተወከሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።