በትምህርት የሚገኝ ዕውቀት በተግባር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት-ዶክተር ካባ ኡርጌሳ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት የሚገኝ ዕውቀት በተግባር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት-ዶክተር ካባ ኡርጌሳ
ጅማ (ኢዜአ) ጥር 06/2015 በትምህርት የሚገኝ ዕውቀት በተግባር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታና የለውጥ ፈር ቀዳጅ መሆን አለበት ሲሉ የቀድሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዓለም አቀፍ ተቋማት ባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ምክትል ቋሚ ተጠሪ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ አስገነዘቡ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ3 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመረቋል።
የቀድሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዓለም አቀፍ ተቋማት ባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ምክትል ቋሚ ተጠሪ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ የዕለቱ የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተዋል።
ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስገነዘቡት በትምህርት የሚገኝ ዕውቀት ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በተግባር የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታና የለውጥ ፈር ቀዳጅ መሆን አለበት ብለዋል።
በሳይንስ በተደገፈ ዘመናዊ ትምህርት የሚገኝ ዕውቀት በተግባር የሁለንተናዊ ለውጥ አመላካችና የለውጥ ፈር-ቀዳጅ መሆን ይጠበቅበታል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተማረ የሰው ሀይልን በማፍራት ለሀገር ግንባታ የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የበለጠ ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥና አሰራር እንዲኖር የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ አንዳይሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ለዕለቱ ተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት በተማሩበት ሙያ ህዝባቸውን በቅንነትና በተማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዶክተር ጀማል አክለውም የህክምና ተመራቂዎች ከራስ ይልቅ ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ የጤና አገልግልት የመስጠት ኃላፊነት አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሪጅስትራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብሩክ ወልደሚካኤል በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 971ዱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ ዲግሪ ካሰለጠናቸው 457 ተማሪዎች ውስጥ 82ቱ ሴቶች እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ ከሰለጠኑ 26 ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች መሀከል 30ዎቹ በዩኒቨርስቲው የትምህርት ዕድል ያገኙ ከሶማሌ ላንድ የመጡ ተማሪዎች መሆናቸውን አቶ ብሩክ ጠቅሰዋል።
በምረቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ታድመዋል።