ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 6/2015 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባዋ ዛሬ ማለዳ በጃንሜዳ የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ሥፍራ ከተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ከነዋሪዎች ጋር በመሆን አፅድተዋል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክትም የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ምናልባት የ3 ሰዎች፤ የቆሙ ሰዎች እና ከቤት ውጪ ምስል

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ ኢትዮጵያን ለዓለም በማስተዋወቅ አበርክቶ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን የጋራ ሃብት በጋራ ጠብቆ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የመዲናዋ ነዋሪዎች ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በጃንሜዳ የተደረገው የጽዳት ዘመቻም መነሻው አብሮነት መሆኑን ጠቁመው፤ በዓሉ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም መልኩ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፤ የጥምቀት በዓል አከባበር ኢትዮጵያን በዓለም የሚያስጠራና እውቅና የተሰጠው የጋራ ሃብት በመሆኑ ለክብረ-በዓሉ ሰላማዊ ክንውን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ለዚህ ደግሞ በዛሬው እለት የታየው ሕብረት ትልቅ ማሳያ መሆኑን የገለጹት ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ ሕብረቱ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በመወከል በጽዳት መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ሼኸ ሰማን መሐመድ፤ የአገር ሃብት የሆነው የጥምቀት በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ከእምነቱ ተከታዮች ውጭ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ትብብር ከዚህ ቀደም የተለመደ መሆኑን የገለጹት ሼኸ ሰማን፤ ይህ ትብብር ዘንድሮም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ-ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ደረጀ ጀንበሩ "ኢትዮጵያ ከኛ የምትፈልገው መለያየትን ሳይሆን አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ነው" ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ ዘመን ያለው ትውልድ በልዩነት ተከባብሮና ተባብሮ በመኖር የአባቶችን ፈለግ መከተል ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

የጥምቀት በዓልን ጨምሮ የመስቀል በዓል፣ የገዳ ሥርዓትና ፍቼ ጫምበላላ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርስነት የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም