ለኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ የሚሆን ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷል-የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ የሚሆን ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷል-የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 6/2015 ለኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ የሚሆን ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ብቻ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ4 ቢሊዮን ብር ስምምነት መደረጉን አመልክቷል።
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከ285 ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን የመመስረት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የስራ እና ክህሎት የስራ እና ስምሪት ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በስድስት ወራቱ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።
"እንደ አገር የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በተደራጀ አግባብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እየታየበት ነው" ያሉት አቶ ንጉሱ፣ ለዚህም የኢንተርፕራይዞች ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የማጠናከርና የማደራጀት ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢንተርፕራይዞቹ የሚያስፈልግ ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አቶ ንጉሱ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በተዘጋጀው መሬት ላይ የሼድ ግንባታን ጨምሮ የብድር አገልግሎት በክልሎቹ በተዋረድ ባሉ መዋቅሮች የሚከናወን ሲሆን ሚኒስቴሩም የተለያዩ የድጋፍ ማዕቀፎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዘርፉ የተስተዋሉ የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያ ትስስር ማነቆዎችን በሂደት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የገንዘብ ችግሩ እንዲቃለል ከሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች ጋር በመነጋገር የአሰራር ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችል ለውጥ መደረጉንም ገልጸዋል።
በእዚህም ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ብቻ ከልማት ባንክ የ4 ቢሊዮን ብር ስምምነት መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
"በሃዋሳ የተዘጋጀው የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከአዲስ አበባ ውጭ መካሄዱ በየአካባቢው ያለውን ዕድል ለማውጣትና ዘላቂ የገበያ ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
ይህንን ጅማሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በማስቀጠል ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ የሚፈጥሩትን የሥራ እድልና የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዜጎች በአካባቢያቸው ያሉ ጸጋዎችን በተቀናጀ መንገድ በመጠቀም ከራስ ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የሀገርን ኢኮኖሚው ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
246 ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራየዞች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር በሃዋሳ ከተማ ሰሞኑን መከፈቱ ይታወቃል።