የኢትዮጵያ የቻን ውድድር ተሳትፎ ጅማሬ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቻን ውድድር ተሳትፎ ጅማሬ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 6/2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) ተሳትፎውን ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።
ከስድስት ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰችው ኢትዮጵያ በዘንድሮ ተሳትፎዋ የተሻለ ግስጋሴ ታደርግ ይሆን?
በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው እና በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት ሰባተኛው የቻን ውድድር ትናንት መጀመሩ ይታወቃል።
በውድድሩ ላይ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አገር አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድላለች።
ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከሞዛምቢክ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ በሁለት የተከፈለ ዝግጅት አድርጓል።
ቡድኑ በአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ ደግሞ በሞሮኮ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
በካዛብላንካ ቆይታው ራሷን ከቻን ውድድር ካገለለችው ሞሮኮ ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጎ 1 ለ 0 እና 2 ለ 1 መሸነፋቸው ይታወሳል።
የዋልያዎቹ ስብስብ ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት አልጄሪያ በማቅናት ለሁለት ቀናት ልምምድ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት አልጄሪያ ከሌሎቹ ተሳታፊ አገራት ቀድሞ በመድረስ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
እባቦቹ(ማምባስ) በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ሞዛምቢኮች አልጀርስ የከተሙት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር።
በ57 ዓመቱ ሞዛምቢካዊ አሰልጣኝ ቺኩዊንሆ ኮንዴ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ በአልጄሪያ የዝግጅት ቆይታው የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል።
ከአልጄሪያው ኤምሲ አልጀርስ ጋር ተጫውቶ 3 ለ 1 ሲሸነፍ ከቤሉዝዳድ ክለብ ወጣቶች ክለብ ጋር ተጫውቶ አሸንፏል።
ሞዛምቢክ በቻን ውድድር ከምትሳተፈው የጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ከቀናት በፊት ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን እስከ 70ኛው ደቂቃ 1 ለ 0 እየመራ ቢቆይም የዕለቱ ዋና ዳኛ ለጋና ፍጹም ቅጣት ምት በመስጠታቸው የሞዛምቢክ አሰልጣኝ ውሳኔውን በመቃወም ተጫዋቾቻቸውን ይዘው ከሜዳ በመውጣታቸው ጨዋታው ተቋርጧል።
የአሰልጣኙ ውሳኔ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ትችት አስከትሎባቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ እርስ በእርስ ሲገናኙ የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ሁለቱ አገራት እ.አ.አ ሕዳር 12/1980 ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ 3 ለ 2 አሸንፋለች።
ዋልያዎቹ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የውድድር ጨዋታዎች አልተሸነፉም። ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
በአንጻሩ ሞዛምቢክ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያሸነፈችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ተሸንፋ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥታለች።
በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 138ኛ እንዲሁም ሞዛምቢክ 114ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በተያያዘ ዜና በቻን ውድድር የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።
በ ‘19 May 1956 Stadium’ ኮትዲቭዋር ከሴኔጋል ከምሽቱ 4 ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በዚሁ ምድብ ከምሽቱ 1 ሰአት የሁለት ጊዜ የቻን አሸናፊዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዩጋንዳ ጋር በተመሳሳይ በ ‘19 May 1956 Stadium’ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።