ቀጥታ፡

ለጥምቀት በዓል ታዳሚዎችን በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል-አስጎብኚ ድርጅቶችና ሆቴሎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 06/2015 የጥምቀት በዓል ታዳሚዎችን በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስጎብኚ ድርጅቶችና ሆቴሎች ገለጹ።

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው። 

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባሻገር ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ በመሆኑ በአገር ሃብትነቱም በልዩ ትኩረትና በድምቀት ይከበራል። 

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እሴትና ትውፊቱን ጠብቆ ከውጭና ከአገር ቤት በሚሰባሰቡ በርካታ እንግዶች እንዲሁም ምእመናን ደምቆ የሚከበር በዓል ነው። 

በመሆኑም የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉን በጥሩ መስተንግዶ ታጅበው ማክበር እንዲችሉ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአስጎብኚዎች ማህበርና የሆቴሎች ማህበራት ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አሸናፊ ካሳ፤ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ በተመዘገበው የጥምቀት በዓል ላይ የሚታደሙ እንግዶችነን በጥሩ መስተንግዶ እንቀበላቸዋልን፤ ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ ከተለያዩ አገራት የጎብኚዎች የጉብኝት ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው በበዓሉ በርካታ እንግዶች እንደሚገኙ እንጠብቃለን ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አስቴር ሰሎሞን በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ታዳሚዎችን በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል ሆቴሎች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አገራት ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ እንግዶችም በተለይም ባለ ኮከብ ሆቴሎች የዋጋ ቅናሽ አድርገው ለጥሩ መስተንግዶ ተዘጋጅተዋል ብለዋል። 

የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም