ቀጥታ፡

አልጄሪያ በአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና ሊቢያን በማሸነፍ በድል ጀመረች

ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ጋር የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች።

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 6/2015 በሰባተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) ትላንት ምሽት በተደረገ የመክፈቻ ጨዋታ በምድብ አንድ አዘጋጇ አገር አልጄሪያ ሊቢያን 1ለ 0 አሸንፋለች።

በዚሁም ምድብ ኢትዮጵያ ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር ትጫወታለች።

በምድብ አንድ በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇ አገር አልጄሪያ ሊቢያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

የ25 ዓመቱ አጥቂ አይሜን ማሂኡስ በፍጹም ቅጣት ምት ለበረሃዎቹ ቀበሮዎች በ57ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቧን አስቆጥሯል።

ከሁለቱ አገራት ጨዋታ በፊት በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ደማቅ የውድድር መክፈቻ ስነ- ስርዓት ተካሄዷል።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እና የአልጄሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አይሜን ቤናብዴራህማኔ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

ናይጄሪያዊው ጄይ ጄይ ኦኮቻ፣ ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ፣ የኮትዲቫሩ ዲዲየር ድሮግባ፣ አልጄሪያዊው ራባህ ማጄር እና ሌሎች የአፍሪካ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቾች በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ታድመዋል።

በምድብ አንድ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰአት በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ጋር የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የወቅቱ የቻን አሸናፊ ሞሮኮ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 17 ዝቅ ብሏል።

የቻን ውድድር እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም