በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጥር 5/2015 /ኢዜአ/ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ቻይና ለኢትዮጵያ የ30 ሚሊዮን ዩዋን የእዳ ስረዛ ማድረጓን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ አዲሱን የአውሮፓዊያን ዓመት በተነቃቃና በተሻለ የዲፕሎማሲ ስራ መጀመሯን ገልጸዋል።
የቻይና፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን በዚህ ረገድ በአብነት ተናግረዋል፡፡
የአዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን ኃ የመጀመሪያ የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ መጀመራቸውንም ገልፀዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የማይዋዥቅ መሆኑን አስረድተው፤
በሁለትዮሽና ቀጠናዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናከራ እንደምትቀጥል መግለፃቸውን ተናግረዋል።
የጀርመን እና ፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጉብኝት በተመለከተም ሁለቱ ሚኒስትሮች አገራቸውን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ህብረትን ጭምር ወክለው የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላት ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ እና እኩል ተጠቃሚነትን መርሕ የተከተለ መሆኑን አስረድተዋል።
የእዳ ስረዛን በተመለከተም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ቻይና ለኢትዮጵያ የ30 ሚሊዮን ዩዋን የእዳ ስረዛ ማድረጓን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
ይህም የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነትን ለማስቀጠል እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
በቀጣይ ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የባህልና የስፖርት ዲፕሎማሲ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አካታች የዲፕሎማሲ አካሄድ እንደምትከተል ገልጸው፤ ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ቁልፍ አገራዊ ተቋሞችን ለስኬታማ የስራ ስምሪት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል።