የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ በኢትዮጵያ ለምን ናረ ?

546

የኢትዮጵያ እግር ኳስ አጀማመር በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ የውጭ አገር መምህራን የእግር ኳስ ቡድኖችን በመፍጠር ውድድሮችን በማድረግ እንደሆነ ይነገራል።

ጨዋታዎችን የሚያደርጉት ትምህርት ቤቶች ሲዘጉና በበዓላት ወቅት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ ።

በዚህ መልኩ ጅማሬውን ያደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በ1920ዎቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ ልጆች 'የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን' በአዲስ አበባ ከተማ አቋቋሙ።

በዚህ መልኩ የተጀመረው እግር ኳስ ተወዳጅነቱ እያደገ መጥቶ በአገሪቱ ከሚዘውተሩ የስፖርት ዓይነቶች በተወዳጅነቱ ከቀዳሚዎቹ አንዱ መሆን ችሏል።

ይሁን እንጂ ስፖርቱ ባስቆጠረው እድሜና በተወዳጅነቱ ልክ ወደፊት መራመድ ተስኖት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከአህጉሪቱ ቡድኖች ጋር አይደለም ከጎረቤት አገራት ጋር መፎካከር እየተሳናት መጥቷል፡፡

በቅርቡ ‘ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና የልማት ፍኖተ ካርታ’ በሚል ርዕስ የቀረበ አንድ ጥናት በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የወጣበትና በቅርቡ በመጽሀፍ መልክ እንደሚታተም የሚጠበቀው ይሄው ጥናት የእግር ኳሱን ችግር በመፍታት አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምዳል ተብሎለታል።

በጥናቱ ላይ በተደረገ ውይይት የክልል እግር ኳስ አመራሮች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።

በ400 ገጾች የቀረበው ጥናት በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን ከነዚህ መካከል የፕሪሚየሪ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች አደረጃጀት፣ የፋይናንስ ስርዓት አሰራርና የተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ ይጠቀሳሉ።

ጥናቱን ያቀረቡት በታውሰን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ጋሻው አብዛ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቁልፍ ችግር የእግር ኳስ ልማት ላይ አለማተኮሩ መሆኑን ነው ያነሱት።

ጥናት አቅራቢው እንደ ችግር ካነሷቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ክለቦች በጀታቸውን ከእግር ኳስ ልማት ይልቅ ለተጫዋቾች ክፍያ ማዋላቸውን ነው።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት ለተጨዋቾች ደሞዝ ብቻ በአማካይ 40 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሲሆን ለአንድ ተጫዎች በአማካኝ በወር ከ130 ሺህ ብር በላይ እንደሚከፍሉ ነው በጥናቱ የተመላከተው።

ይህ ክፍያ ከአፍሪካ አገራት በሊግ ደረጃቸውና አደረጃጃታቸው ከኢትዮጵያ የተሻሉ ከሚባሉት በርካታ አገራት እጅግ የላቀ ነው።

የደሞዝ ክፍያውን በንጽጽር ያስቀመጡት ዶክተር ጋሻው በኢትዮጵያ የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ከፍያ በአማካኝ 2 ሺህ 667 ዶላር እንደሆነና በ50 ብር ምንዛሪ ሲታሰብ 133 ሺህ ብር ገደማ እንደሆነ አስረድተዋል ።

በጋና የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ክፍያ በአማካኝ 1 ሺህ ዶላር ሲሆን በናይጄሪያ ደግሞ 1 ሺህ 250 ዶላር መሆኑን ጥናቱ ሲያመላክት በኬኒያ በአማካኝ 800 ዶላር መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የክለብ ተጫዋቾች ደሞዝ ከሌሎች አገራት ጋር በንጽጽር ሲታይ በእግር ኳስ ደረጃቸው የተሻሉ ከሆኑ ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ጭምር ከእጥፍ በላይ እንደሚሆን ጥናቱ አመልክቷል።

የውጭ አገራት አብዛኛዎቹ የእግር ኳስ ክለቦች ገቢያቸውን የሚያመነጩት ከስፖንሰር አድራጊዎች፣ ከቲሸርትና ማልያ ሽያጭ እንዲሁም ከሜዳ መግቢያ ትኬት ሽያጭ መሆኑ ይታወቃል ።

በኢትዮጵያ ፕሪሚሪ ሊግ ከሚሳተፉት 16 ክለቦች ከኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ በስተቀር ሌሎቹ 14 ክለቦች ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ የመንግስት ካዝና ነው።

ከመንግስት ካዝና በሚወጣው ገንዘብ ከሚንቀሳቀሱት ቡድኖች መካከል ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኞቹ ገንዘቡን ምን ላይ እንደዋሉት የሚያሳይ ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት እንደሌላቸው ነው ጥናት አቅራቢው የጠቀሱት ።

ይህ ተግባር በእግር ኳሱ ልማት የጎላ ተሳትፎ የሌላቸው ግለሰቦች ያለምንም ልፋት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

ክለቦች የፈለጉትን ተጫዋች በፈለጉት የደሞዝ መጠን የማስፈረም መብት ቢኖራቸውም የክፍያ ስርዓታቸውን መፈተሽ ግን የግድ ያስፈልጋል።

ለአንድ ተጫዋች ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ከፈለጉ የመንግስትን ድጎማ ከመጠበቅ በመውጣት በራሳቸው ገቢ ማመንጨት የሚችሉበትን ፕሮጀክት መቅርጽ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ይህን ማድረግ ከቻሉ ክለቦች ከሚያገኙት ሃብት ላይ የፈለጉትን ተጨዋች በፈለጉት ክፍያ ማስፈረም እንደሚችሉ ነው በጥናቱ እንደ መፍትሄ የተቀመጠው።

ቡድኖች የገንዘብ ምንጫቸውን ከማስፋት ባለፈ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መከተል እንደሚጠበቅባቸው ነው ጥናቱ የሚያስቀምጠው ።

ከዚህ በተጨማሪ ከዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አስገዳጅ በሆነ መልኩ ሌሎች ወጪያቸውን በመቀነስ የእግር ኳስ ልማት ስራዎችን እንዲያከናወኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ መናር በቀጣይ የክለቦችን ህልውናን ጭምር የሚፈታተን እንደሆነ አንስተዋል።

ለተጫዋቾች ወርሃዊ ደመወዝ ይከፈላል የሚባለው ገንዘብ በቀጥታ ለተጫዋቾች እንደማይደርስ የገለጹት ተሰብሳቢዎቹ እግር ኳሱ አካባቢ ያሉ አመራሮችና ደላሎች የገንዘቡ ተካፋይ መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል።

በመሆኑም መንግስት ለእግር ኳሱ የሚያደርገውን ድጋፍ በመቀነስ በእግር ኳሱ ልማት ላይ ማተኮር እንዳለበትና የሚታየውን የተጋነነ ክፍያና ሌብነት መቆጣጠር እንደሚገባ ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም