ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሰሜን ምስራቅ፤ የሰሜን ምዕራብ፤ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የተወሰኑ አካባቢዎች መጠነኛ ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሰሜን ምስራቅ፤ የሰሜን ምዕራብ፤ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የተወሰኑ አካባቢዎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አስር ተከታታይ ቀናት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚኖረው የደመና ሽፋን ሳቢያ በሰሜን ምስራቅ፤ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የተወሰኑ አካባቢዎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚያስተናግዱ ገልጿል፡፡

በዚህም ከአማራ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፤ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፤ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች፤ የአፋር ዞን 2 እና 4፤ የመካከለኛው ምዕራብ ትግራይ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ጅማ፤ ኢሉአባቦር፤ ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮጉድሩ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቤንች ሸኮ፤ የሸካ እና ከፋ ዞኖች ተመሳሳይ የአየር ፀባይ የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፤ ፀሃያማ እና ነፋሻማ የአየር ፀባይ ሁኔታ የሚያስተናግዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ደጋማ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱ ቅዝቃዜ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ኢንስቲትዩት የገለጸው፡፡

እርጥበታማ የአየር ሁኔታን በሚያስተናግዱ አካባቢዎች በበልግ ወቅት አስቀድመው እርሻ ለሚጀምሩ ቦታዎች ማሳን ለማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የተጠቆመው፡፡

በተመሳሳይ በላይኛው እና በመካከለኛው አባይ፤ ባሮ፤ አኮቦ፤ የመካከለኛው እና የታችኛው ኦሞ ጊቤ፤ ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም ተከዜ የሚገኙ ተፋሰሶች ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም ደረቃማ የአየር ሁኔታን በሚያስተናግዱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የሰበሰቡአቸውን ሰብሎች ለመውቃትና ምርቶቻቸውን ያለብክነት በማከማቸት ወደ ገበያ ለማውጣት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስታውቋል፡፡

ከደረቃማው የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በሚያስተናግዱ አካባቢዎች ላይ በመስኖ በሚለሙ የፍራፍሬ ተክሎች፣ በጓሮ አትክልቶች እና በአንዳንድ የቤት እንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል ኀብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም