ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ32 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ32 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
ጥር 05/2015(ኢዜአ). የኢትዮጵያ መንግስት እና የፈረንሳይ መንግስት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ32 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪኔ ኮሎና ተፈራርመዋል፡፡
ድጋፉ በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት እና የአርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና በሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ እንደሚውል ተገልጿል።
በሁለት ምዕራፍ የሚደረገው ድጋፉም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ በመገንባት 12 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በግጭት ምክንያት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችን ጨምሮ 400 ሺህ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን በሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተጠቅሷል።
በዚህም የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ 28 ሚሊየን ዮሮ እንዲሁም አውሮፓ ህብረት ደግሞ የ4 ሚሊየን ዮሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል።
በስምምነት ፊርማው የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ፣ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።
መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡