ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 05/2015 ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲን የተመለከተ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ኢትዮጵያ አዲሱን የአውሮፓውያን ዓመት በተነቃቃና በተሻለ የዲፕሎማሲ ስራ መጀመሯን የቻይና፣ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ ስራ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ መካሄድ ኢትዮጵያ ሰላሟ ተረጋግጦ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ኃላፊነት እንድትወጣ የሚያስችላት እንደሆነም መግለጻቸውን አክለዋል።

ይህ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በበጀት ዓመቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው በቀጣይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህልና ስፖርት ዲፕሎማሲ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አካታች የዲፕሎማሲ አካሄድ እንደምትከተል ገልጸው ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ቁልፍ አገራዊ ተቋሞችን ለስኬታማ የስራ ስምሪት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓለማቀፋዊ ፈተናዎችን እንዲሻገር ከውስጣዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ጎረቤት አገራት ላይ በማተኮር እንደሚሰራና ኢትዮጵያን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናነወኑ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም