ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የምታከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ ፈረንሳይና ጀርመን ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 05/2015 ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን የምታከናውናቸውን ተግባራት የፈረንሳይና ጀርመን መንግስታት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

የጀርመን የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክና የፈረንሳይና የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎናን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የሰላም ስምምነቱን አተገባበር በማድነቅ የመንግስትን ጥረት ለመደገፍ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረው በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ስልክ፣ ባንክና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ መጀመራቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

መንግስት በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ የመልሶ መቋቋምና ተሃድሶ ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸው፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት ይህንኑ ስራ እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ አዲስ ምእራፍ የምንከፍትበት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኢኮኖሚያችንን ወደፊት ለማራመድና የኀብረተሰቡን ፍላጎት ለመመለስ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከአውሮፓ ህብራትና አባል አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ለማሻሻል እንሰራን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ያወጡትን የጋራ ሪፖርት ተከትሎ መንግስት የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ- ኃይል በማቋቋም በሪፖርቱ ለቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ስመጥር የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳላት ጠቅሰው፤ "በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኤክስፐርት እንዲመድብ ጋብዘናል" ብለዋል፡፡

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት መንግስታት የአውሮፓ ህብረትን ጨምረው ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የኢኮኖሚ ትብብራችንን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የፈረንሳይ የአውሮፓ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎናም ኢትዮጵያ በቀጠናው እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን ተናግረው ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ሁለንተናዊ ግንኙነት ዘላቂ በሆነ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መገንባት እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ለአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ካውንስል ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡም ሚኒስትሮቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም