ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ከሁለትዮሸ ባሻገር በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ከሁለትዮሸ ግንኙነት ባሻገር በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር ገለጹ።

ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል።

ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅ ባደረጉት ተጋድሎ የነጻነት አባት በመባል የሚታወቁት ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸው የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት አመላካች ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በንግድ፣ በኢንቨስትመት፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና በሌሎች ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት መድረክ ከማስተናገድ ባሻገር ሂደቱ ምቹ እንዲሆን ደቡብ አፍሪካ የላቀ ሚና መወጣቷን አስታውሰዋል።

በዚህም የሰላም ስምምነቱ "ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በማመንጨት" ስኬት የተመዘገበበት መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለመመስረት እንቅስቀሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት ከሁለትዮሸ ግንኙነት በተጨማሪ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የጋራ አቋም በመያዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ አምባሳደር ሙክታር አክለዋል።

ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድ ስርዓት ያስከተለባቸውን ችግሮች በውይይት በመፍታት የተሻለች አገር መገንባት መቻላቸውን ገልጸው፤ ይህ ልምድ ኢትዮጵያ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ለምታደርገው ጥረት የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይ ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሚጠቅም በመሆኑ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ዘርፈ ብዙ ልምዶችን እንደምትቀስም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም