የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) ጉዞ ከአቢጃን እስከ አልጀርስ

27

እ.አ.አ መስከረም 11 ቀን 2007 ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮናን ለመጀመር ሀሳብ የተጠነሰሰበት ዕለት ነበር።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ለአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድናቸውን ወክለው የመጫወት እድል እንዲያገኙ እና የሊግ ውድድራቸውን ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቅን ታሳቢ ያደረገ የቻን ውድድር ፎርማት ይፋ አደረገ።

የቻን ውድድር ሀሳብ እ.አ.አ ጥር ወር 2008 የፀደቀ ሲሆን ካፍ ኮትዲቭዋር የመጀመሪያውን የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ መረጣት።

የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የመጀመሪያው የቻን ውድድር እ.አ.አ የካቲት 22 እስከ መጋቢት 8 ቀን 2009 ተካሄደ።

አዘጋጇን ኮትዲቭዋርን ጨምሮ፣ሴኔጋል፣ጋና፣ሊቢያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ታንዛንያ፣ ዛምቢያ ዚምባቡዌ በውድድሩ ላይ የተሳተፉ አገራት ናቸው።

እ.አ.አ የካቲት 22 በፍሊክስ ሁፔት በተደረገው የመጀመሪያው የቻን በምድብ አንድ ዛምቢያ ኮትዲቭዋርን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ጊቭን ሲንጉሉማ የቻን ውድድርን የመጀሪያውን ግብ አስቆጠረ። ሲንጉሉማ በጨዋታው ሶስት ግቦችን በማስቆጠር የወድድሩን የመጀመሪያውን ሀትሪክ በመስራት በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፈረ።

እ.አ.አ መጋቢት 8 ቀን 2009 35ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ፍሊክስ ሁፑት ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ጋናን 2 ለ 0 በመርታት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ዋንጫ አነሳች።

Les léopards locaux vainqueurs de la première édition du CHAN (8 mars 2009, Abidjan)

አሌይን ካሉዪቱካ እና ቤዲ ምቤንዛ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በደረጃ ጨዋታ ዛምቢያ ሴኔጋልን 2 ለ 1 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሱዳን አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2011 የተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና የተሳታፊዎች ቁጥር ከ8 ወደ 16 ከፍ ያለበት ነበር።

ከ16ቱ አገራት 11ዱ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን የተቀሩት አምስት አገራት ቀድም ብሎ በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

ሴኔጋል፣ጋና፣ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ኮትዲቭዋር እና ዚምባቡዌ በመጀመሪያው ሻምፒዮና የተሳተፉ አገራት ናቸው።

እ.አ.አ የካቲት 25 ቀን 2011 በአልሜሪክ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ቱኒዚያ መጅዲ ትራኡይ፣ ዙሄር ዳኡአዲ እና ኡሳማ ዳራጊ ባስቆጠሯቸው ግቦች አንጎላን 3 ለ 0 በመርታት ዋንጫውን አነሳች።

አዘጋጅ አገር ሱዳን አልጄሪያን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ሶስተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና እ.አ.አ. በ2013 እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት ነበር።

ይሁንና የአውሮፓ ክለቦች ውድድሩ ከፊፋ ዓለም ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር ሰሌዳ ጋር እንዳይጋጭ በአንድ ዓመት ዘግይቶ ይካሄድ በሚል ያቀረቡት ጥያቄ በካፍ ተቀባይነት አግኝቶ ውድድሩ እ.አ.አ 2014 ተደረገ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ሊቢያ እ.አ.አ 2014 የቻን ውድድርን እንድታዘጋጅ መርጧት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በአገሪቷ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከአስተናጋጅነቷ ሰርዟታል።

ሊቢያ የቻን ብቻ ሳይሆን የ29ው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነትንም ጭምር ነው ያጣቸው።

በርካታ አገራት ውድድሩን ለማዘጋጀት ጥያቄ ቢያቀርቡም ደቡብ አፍሪካ ውድድሩን እንድታሰናዳ በካፍ ተመረጠች። 19ኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ ስትዘጋጅ የገነባችው መሰረተ ልማት ተመራጭ አድርጓታል።

ሶስተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና እ.አ.አ ከጥር 11 አስከ የካቲት 1 ቀን 2014 ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችበት ነበር።

ኢትዮጵያ በወቅቱ በምድብ ሶስት ከጋና፣ሊቢያ እና ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ(ኮንጎ ብራዛቪል) ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ከሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ ጋር ሲሆን 2 ለ 0 ተሸንፏል።

በቀጣይ ጨዋታዎች በሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና ጋና በተመሳሳይ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።

ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ ያለ ምንም ነጥብ በአራት የግብ እዳ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

ሊቢያ እና ጋና ለፍጻሜው ደርሰው ሊቢያ በመለያ ምት 4 ለ 3 አሸንፈው ዋንጫ በማንሳት በጦርነት ለተጎዳው ሕዝብ ትልቅ ስጦታን አበረከቱ።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው።

በደረጃ ጨዋታ ናይጄሪያ ዚምባቡዌን 1 ለ 0 በመርታት ሶስተኛ ወጥታለች።

ከሶስተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና አንስቶ ውድድሩ ሙሉ ቁጥር በሚሆንባቸው ዓመታት መካሄድ ጀመረ።

ርዋንዳ የአራተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና አዘጋጅ አገር ናት። ውድድሩ የተካሄደው ከእ.አ.አ ጥር 16 እስከ የካቲት 7 ቀን 2016 መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተሳትፋለች።

ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ካሜሮን እና አንጎላ ጋር ተደለደለች።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ 3 ለ 0 ተሸነፈ።

በቀጣዩ ጨዋታ ከካሜሮን ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ በመለያየት በውድድሩ ተሳትፎው የመጀመሪያ ነጥቡን አገኘ።

በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ዋልያዎቹ በአንጎላ የ2 ለ 1 ሽንፈት ገጠማቸው።

በሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት ወደ ጥሎ ማለፍ ማለፍ አልቻለም።

በፍጻሜው ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ማሊን 3 ለ 0 በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮና መሆን ቻለች።

ኮትዲቭዋር ጊኒን 2 ለ 1 በመርታት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች።

አምስተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ያዘጋጀችው በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አስደናቂ ግስጋሴ ያደረገችው ሞሮኮ ናት።

እ.አ.አ በ2018 የተሰናዳውን ውድድር ኢትዮጵያ የማዘጋጀት እድሉን አግኝታ የነበረ ቢሆንም መንግስት ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን የማረጋገጫ ደብዳቤ ለካፍ ባለመላኩ ምክንያት አስተናጋጅነቷን ተነጥቃለች።

እ.አ.አ የካቲት 4 ቀን 2018 በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኮ ዛካሪያ ሀድራፍ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች እንዲሁም ዋሊድ ኤል ካርቲ እና አዩብ ኤል ካቢ ከመረብ ላይ ባሳረፉበት ግብ ናይጄሪያን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በመርታት ዋንጫውን አገሯ ላይ አስቀረች።

ሱዳን ሊቢያን በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ከሰሜን አፍሪካ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አመራ። ካሜሮን ስድስተኛውን የቻን እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ. ከጥር 16 እስከ የካቲት 7 ቀን 2020 አካሄደች።

እ.አ.አ የካቲት 7 ቀን 2020 ከ42ሺህ በላይ ተመልካች በሚያስተናግደው አህመዱ አሂጆ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኮ ሶፊያን ቡፍቲኒ እና አዩብ ኤል ካቢ ባስቆጠሯቸው ግቦች ማሊን 2 ለ 0 በመርታት ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን አነሳች።

አዩብ ኤል ካቢ በሁለት የቻን የፍጻሜ ጨዋታዎች ግብ በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጫዋች መሆን ቻለ።

ጊኒ አዘጋጅ አገር ካሜሮንን 2 ለ 0 በመርታት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን አጠናቃለች።

እስከ አሁን በተደረጉ ስድስት የቻን ውድድሮች ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና ሞሮኮ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዘዋል።

ቱኒዚያ እና ሊቢያ አንድ አንድ ጊዜ ዋንጫውን አንስተዋል።

ማሊ እና ጋና በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ፍጻሜ ደርሰው የተሸነፉ አገራት ናቸው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አልጄሪያ ከጥር 13 እስከ የካቲት 4 ቀን 2023  በምታዘጋጀው ሰባተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ከዛሬ ጀምሮ ለ23 ቀናት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አገር አልጄሪያ፣ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም