ጠንካራ መሰረት ያለውን የኢትዮጵያና ካናዳ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ መሰረት ያለውን የኢትዮጵያና ካናዳ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ጥር 05/2015 (ኢዜአ) ጠንካራ መሰረት ያለውን የኢትዮጵያና ካናዳ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናገሩ።
ኢትዮጵያና ካናዳ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ ወዳጅነት አንዳላቸው የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
ለግንኙነቱ መጀመር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1954 አፄ ኃይለሥላሴ በካናዳ ቶሮንቶ ያደረጉት የአጭር ጊዜ ጉብኝት ይጠቀሳል፡፡
ለዚህም በ1967 ዓ.ም ለሁለት ሳምንታት ያደረጉት ጉብኝት ግን ግንኙነቱ ይፋዊ መልክ ያስያዘ እንደነበር ሰነዶች ያመላክታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአብሮነትና ወንድማማችነት መርህ የተመሰረተው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ የተጣለ ሰለመሆኑ ይነገራል።
በኢትዮጵያና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ሁለቱ ሀገራት በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ መድረክ ዲፕሎማሲ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ካናዳ በተለይ በንግድ፣ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት፣ አቪየሽን፣ ማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት ይህን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር የሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ የስልክ ውይይቶች የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ጥንካሬ ሌላኛው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ በተፈተነችባቸው ባለፉት ዓመታት ካናዳ ሚዛናዊ አቋም ስታራምድ መቆየቷን አንስተው፤ ይህም የአገራቱን ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመደገፍ ረገድም የበኩሏን ሚና መወጣቷን ነው የተናገሩት፡፡
ይህን በጠንካራ መሰረት ላይ የተጣለ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር በትብብር እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
ካናዳ በመንግስትና ህወሃት መካካል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ያላትን ድጋፍ መግለጿን ጠቅሰው፤ በሀገር ቤት የመጣው ሰላም በዲያስፖራው መካከል እንዲጠናከር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።