የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት በህክምና ላብራቶሪ፣ በፍተሻና ንጽጽር ዘርፍ ለ11 ተቋማት የላቀ የብቃት ማረጋገጫ ዕውቅና ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት በህክምና ላብራቶሪ፣ በፍተሻና ንጽጽር ዘርፍ ለ11 ተቋማት የላቀ የብቃት ማረጋገጫ ዕውቅና ሰጠ
አዳማ ጥር 05/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት በህክምና ላብራቶሪ፣ በፍተሻና ንጽጽር ዘርፍ ለ11 ተቋማት የላቀ የብቃት ማረጋገጫ ዕውቅና ሰጠ።
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት ተሰማ እንደገለፁት የላቀ ብቃት የጥራት ማረጋገጫ አክሬዲቴሽን የተሰጣቸው በህክምና ላቦራቶሪ እንዲሁም በፍተሻና ካሊብሬሽን፣ የሚጠበቅባቸውን የሙያና ክህሎት ደረጃ መድረሳቸው ለተረጋገጠ ተቋማት ነው።
በዚህም የአሰራርና መሰረተ ልማት የምዘና መስፈርቱን ላሟሉ 11 ተቋማት አክሬዲቴሽን እንደተሰጠ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማህበር፣ የሸጋው ሞጣ ጄነራል ሆስፒታልና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል ትናንት በአዳማ አክሬዲቴሽን ከተሰጣቸው መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የብሔራዊ የሳንባ ነቀርሳ ላቦራቶሪና የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም የላቀ የጥራት ማረጋገጫውን ካገኙት መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የጥራት ማረጋገጫው የሀገር ውስጥና የወጭ ምርቶች ጥራትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲዘምኑ እንዲሁም ምርትና ምርታማነት ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
ተቋሙ እየሰጠ ያለው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተቀባይነት ያለው መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ትብብር የአሰራር ስርዓት ሰርቲፊኬሽን አገልግሎቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱንም አክለዋል።
በዚህም በህክምና፣ በፍተሻና ካሊብሬሽን እንዲሁም በአሰራር ስርዓት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
በሀገሪቷ ከ13 ሺህ በላይ ደረጃዎች የተዘጋጁና 306 አስገዳጅ ደረጃዎች መኖራቸውን የገለፁት ወይዘሮ መሰረት፤ ከጤና፣ ከወጭና ገቢ ንግድ እንዲሁም ከአካባቢ ደህንነት አንፃር በትክክል እየተተገበሩ መሆኑን የምናረጋግጠው በአክሬዲቴሽን ነው ብለዋል።
አሁን የተሰጠው የላቀ ብቃት የጥራት ማረጋገጫ አክሬዲቴሽን ለአራት ዓመት የሚቆይ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ዕውቅና ያገኙበትን ሂደት ጠብቀው እያመረቱና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ግን በየዓመቱ በሶስተኛ ወገን ይገመገማል ብለዋል።
አገልግሎቱ እስከ አሁን ለ112 ተቋማት የምርትና አገልግሎት ጥራት የአክሬዲቴሽን ዕውቅና የሰጠ ሲሆን 116 የፍተሻ ወሰኖችን ማካተቱንም ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር የጥራት ላቦራቶሪ ስራ አስኪያጅ አቶ ደነቀ ነጋሽ እንደገለፁት የጥራት ላቦራቶሪ ዕውቅና ያገኘነው በክርና በጨርቅ ላይ በሰራነው ዘጠኝ መላኪያዎች ነው ብለዋል ።
ጥራትን አሟልተን ይሄን ዕውቅና ማግኘታችን በሀገር ውስጥ ገበያም ሆነ ወደ ውጭ የምንልከው ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት ያለውና ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል ።
በተጨማሪም በቀጣይ ግብዓት የምንጠቀመው ምርት በተቀመጠው ምዘና መሰረት በላቦራቶሪ ፈትሸን ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የቢሌስ ፉድ ኮምፕሌክስ ላቦራቶሪ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ አወቀ በበኩላቸው በምግብና መጠጥ የምርት ጥራት አክሬዲቴሽን ዕውቅና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
እውቅናውም የግብርናና አግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል ።