ቀጥታ፡

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ዛሬ ይጀመራል።

በውድድሩ መክፈቻ አስተናጋጅ አገር አልጄሪያ ከሊቢያ ከምሽቱ 4 ሰዓት 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ አገራት የውድድር እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ጨምሮ እርስ በእርስ ሲገናኙ የዛሬውን ጨምሮ ለ19ኛ ጊዜ ነው።

May be an image of 10 people, people standing, outdoors and text that says 'EFFO'

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 18 ጨዋታዎች አልጄሪያ 10 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሊቢያ ሶስት ጊዜ አሸንፋለች።

አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በ18ቱ ጨዋታዎች አልጄሪያ 25 እንዲሁም ሊቢያ 13 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሁለቱ አገራት ሞሮኮ እ.አ.አ 2018 ባዘጋጀችው አምስተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና ለማለፍ በ2017 ባደረጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ ሊቢያ አልጄሪያን በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ለውድድሩ ማለፏ የሚታወስ ነው።

ሊቢያ በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ 1 ስታሸንፍ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ አንድ አቻ ተለያይታለች።

May be an image of outdoors

በ46 ዓመቱ የአልጄሪያ እና ፈረንሳይ የጥምር ዜግነት ባለቤት በሆኑት ጃሜል ቤልማዲ የምትሰለጥነው አልጄሪያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት እግር ኳስ ደረጃ 40ኛ ላይ ነች።

በአንጻሩ በ53 ዓመቱ ፈረንሳዊ ኮሬንቲን ማርቲንስ የምትመራው ሊቢያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 120ኛ ላይ ትገኛለች።

ከአልጄሪያ እና ሊቢያ ጨዋታ በፊት በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም የመክፈቻ ስነ ስርዓት ይካሄዳል።

በቻን ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ነገ ከቀኑ 10 ሰአት በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከሞዛምቢክ አቻው ጋር ይጫወታል።

ሞሮኮ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 17 ዝቅ ብሏል።

የአትላንስ አንበሶች ይገኙበት በነበረው ምድብ ሶስት ጋና፣ማዳጋስካር እና ሱዳን ተደልድለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም