ባለፉት አምስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ32 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

26

አዲስ አበባ ጥር 05/2015(ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ተቋሙ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት ለሱዳንና ጅቡቲ ከቀረበ የኤልክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ለሁለቱ ሀገራትም በጥቅሉ ከ580 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤልክትሪክ ኃይል አቅርቦት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ የኤልክትሪክ ሃይል ለማቅረብ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት መሰረት ኃይል ማቅረብ መጀመሯንም ገልጸዋል፡፡

በአምስት ወራት የተገኘው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በተወሰነ መልኩ መቀነስ ማሳየቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኃይል ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ በቀጣይም ለሚቀርቡ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡”

የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ሲጠናቀቁ በፍጥነት እያደገ ለመጣው የአገር ውስጥና የጎረቤት አገራት ኃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት ይቻላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም