ቀጥታ፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ የአምባሰሏን ንግሥት የአርቲስት ማሪቱ ለገሰን የክብር ዶክተሬት አስረከበ

ደሴ ኢዜአ ጥር 4/2015 ወሎ ዩኒቨርሲቲ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ለአበረከተችው የአምባሰሏ ንግሥት አርቲስት ማሪቱ ለገሰን የክብር ዶክተሬት አስረከበ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የወሎ ባህልና እሴት ጎልብቶ ለትውልድ እንዲተላለፍ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ነው።

ለሀገር መሰረት ለጣሉ ባለውለታዎችን በማክበር የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ለማፍራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ወሎን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከማስተዋወቅ ባለፈ ለኢትዮጵያውያን አንድነት ጉልህ ሚና በመጫወቷ የክብር ዶክትሬት መስጠቱን ተናግረዋል።

ለዚህም የዩኒቨርስቲው ሴኔት ሰኔ 2008 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመስጠት ወስኖ እንደነበር አስታውሰው፤ በወቅቱ ሀገር ውስጥ ባለመኖሯ ምክንያት ዛሬ እንዲሰጣት ተደርጓል ብለዋል።

አርቲስት ማሪቱ ከልጅነት እድሜዋ ጀምራ በጥበብ የኖረች ተወዳጅ በመሆኗ ዩኒቨርስቲው ያክብራታል፣ ያደንቃታልም ብለዋል።

የአርቲስቷ የቀድሞ የስራ ባልደረባ አርቲስት መሃመድ ይመር አርቲስቷ በተለያዩ ስራዎቿ ተወዳጅነትን ያተረፈች፣ ሀገሯን የምትወድ፣ ለጥበብ መሠረት የጣለች ነች ብሏል።

ዩኒቨርስቲው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱ ተተኪ ትውልድ ለማፍራትና ጥበብ ቦታ እንዲያገኝ ድርሻው የጎላ መሆኑንም ተናግሯል።

አርቲስት ማሪቱ ለገሰ በበኩሏ ለተሰጣት ክብር አመስግና ስራዋን አጠናክራ ለመቀጠል ብርታት እንደሚሆናት ገልጻለች ።

አክላም ከ23 ዓመታት የውጪ ሀገር ቆይታዋ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገላት አቀባበልና ለሰጣት ክብርም አመስግናለች።

አርቲስቷ የአምባሰሏ ንግሥት፣ የቅኝቶች እናት፣ የባህል ሙዚቃ ንግሥት፣ ማሬዋ የሚሉና ሌሎች ቅጥያ ስሞችንም አግኝታለች።

በክብር ዶክትሬት አሰጣጡ ስነ ስርዓት ላይ ከፌዴራል፣ ከመቅደላ፣ ከወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች፣የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ ባልደረቦቿና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም