የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትውልድ ቅብብሎሽ በርካታ የአገር ባለውለታ ጀግኖችን እያፈራ ያለ ተቋም ነው - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትውልድ ቅብብሎሽ በርካታ የአገር ባለውለታ ጀግኖችን እያፈራ ያለ ተቋም ነው - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትውልድ ቅብብሎሽ በርካታ የአገር ባለውለታ ጀግኖችን እያፈራ ያለ ታሪካዊ ተቋም መሆኑን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል በደረጃ-7 የሙያ ማሻሻያ ያደረጉ የአየር ኃይል ነባር አባላትንና ለመጀመሪያ ጊዜ ለስድስት ወራት መሰረታዊ የውትድርና ሥልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ምልምል ወታደሮችን አስመርቋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እና የአየር ኃይል ከፍተኛ መኮንኖች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
ዋና አዛዡ አክለውም በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የተቋማት ግንባታ ታሪክ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እድሜ ያስቆጠረና በትውልድ ቅብብሎሽ ጀግኖችን እያፈራ የመጣ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
የሰው ኃይል እና መሰረተ-ልማት ግንባታን ጨምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሟላ ትጥቅ ያለው ጠንካራ ተቋም በመፍጠር በትውልድ ቅብብሎሽ ጀግና የማፍራት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አረጋግጠዋል።
ምሩቃኑም የወሰዱትን የተሟላ መሰረታዊ የውትድርና ጥበብ የቀጣይ የበረራ እና ቴክኒሻንነት ሥራቸውን ከተቋሙ እሴት ጋር በማዛመድ አገራቸውን በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኃይል አካዳሚ ኮሎኔል ገዛኸኝ ነጋሽ፤ አካዳሚው ከ1940 ዎቹ ጀምሮ ጀግና እና ስመ-ጥር ሙያተኞችን በማፍራት የኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
አሁንም የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በጀግንነት የሚፈጽሙና የአገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎችን በጥራትና ብቃት እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።
አየር ኃይሉ ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ የሰው ኃይል ለማሟላት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ በአየር ኃይል አካዳሚ የአመራር ትምህርት ቤት ኃላፊ
ሌተናል ኮሎኔል ደረጄ ደጀኔ ናቸው።
ለአየር ኃይል አካዳሚ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ሻምበል ፈቃዱ ገለቱ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ በስነ-ልቦና እና በአካል ጥንካሬ እንዲላበሱ የሚያደርግ የተለያየ ወታደራዊ ትምህርቶችን ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ምሩቃን ምልምል ወታደሮቹ አገርና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት በመወጣት አገራቸውን ከማንኛውም ጠላት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በቆይታቸው የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው ምሩቃንም ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ የእውቅና ሰርተፊኬት የተረከቡ ሲሆን አገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት ለማገልገል ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።
የምርቃት መርሃ-ግብሩ በአየር ኃይል ዋና መምሪያ ቅጥር ግቢ በድምቀት ተካሂዷል።