በከተሞች የትብብር መድረክ ለልማት ማፋጠንና መልካም አስተዳደር መስፈን እገዛ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች የትብብር መድረክ ለልማት ማፋጠንና መልካም አስተዳደር መስፈን እገዛ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል
ደብረ ማርቆስ፤ ጥር 4 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ለከተሞች ልማት ማፋጠንና መልካም አስተዳደር መስፈን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ የከተሞችን እድገት ለማፋጠን የሚያግዝ አውደ ጥናት በደብረማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የመድረኩ ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጤናው በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ የትብብር መድረኩ ከተሞች እርስ በእርስ ተደጋግፈው የተሻለ እድገት እንዲያመጡ ታስቦ የተቋቋመ ነው።
በትብብር መድረኩ ከ80 በላይ ከተሞችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ገልጸው፤ የስማርት ሲቲ ጽንስ ሀሳብን ተግባራዊ እንዲሆን በሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የፈጻሚ አካላትን የክህሎት ክፍተት በመሙላት ለከተሞች ልማት ማፋጠንና መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተው አባል የሆኑ ከተሞች በሰው ሃይልና በልምድ ልውውጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈም የሚስተዋልባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር በተደራጀ አግባብ ለመፍታት የትብብር መድረኩ እያገዘ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀ በበኩላቸው ፤ የኢትዮጵያ የከተሞች ትብብር መድረክ የከተሞችን የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ብሎም ፈጣን እድገት ለማምጣት አንዱ ካንዱ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተለይም ከተሞች የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከኋላ ቀር አሰራሮች ወጥተው ዘመናዊነትን እንዲከተሉ ከፍተኛ አስተዋጥኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ከተማዋን በስማርት ሲቲ ጽንስ ሀሳብ ለነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ከሙስና የፀዳ አሰራር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።
የስማርት ሲቲ ጽንስ ሀሳብ አንዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማዘመን የመታወቂያ አሰጣጡን በዲጂታል ለማድረግ በተሞክሮ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በመነሳትም በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም ቀበሌዎች ተደራሽ በማድረግ ከዚህ ጋር ተያይዞ ይስተዋል የነበረው የመልካም አስተዳደርና ያለአግባብ የመታወቂያ አሰጣጥ ችግር እንደሚቃለል ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመሬት አስተዳደር ክፍሉን የፋይል አያያዝ ስርዓት በቴክኖሎጅ እንዲታገዝ እየተደረገ ነው ብለዋል።