በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከ1 ነጥብ 36 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከ1 ነጥብ 36 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከ1 ነጥብ 36 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የዳያስፖራዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ባለፉት አራት ዓመታት ትልቅ ለውጥ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የልማትና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዳያስፖራዎች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በሃዋላ አገልግሎት ከውጭ ወደ አገር ቤት በሚልኩት ገንዘብም ገቢ በማስገኘት የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ብቻ ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ከ1 ነጥብ 36 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት 121 ዳያስፖራ ባለሃብቶች በወጪና ገቢ ንግድ ላይ የተሰማሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ችግር በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ ማግኘቱን ተከትሎ የዳያስፖራዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በቀጣይ የሚከበሩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት የመምጣት ዕቅድ ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መሐመድ፤ በቆይታቸው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሚጠቅሙ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል ብለዋል።
በአገር ልማትና የሰላም ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማጠናከር ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የድርሻቸውን ማበርከታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የዳያስፖራ አባላት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም የእውቅና መርሃ-ግብር እየተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል።