ቀጥታ፡

ብሄራዊ ባንክ በወርቅ መግዣ ዋጋ ላይ ያደረገው ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል-የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በወርቅ መግዣ ዋጋ ላይ ያደረገው ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ እና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት የሚያስችል መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታት በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የወርቅ መግዣ ዋጋ 35 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ለመግዛት መወሰኑ ይታወሳል። 

የተደረገው ማበረታቻ በህገ-ወጥ መንገድ እየተፈተነ ላለው የወርቅ ግብይት ምን ፋይዳ አለው? ዘርፉ በምን መልኩ ሊደገፍ ይገባል? የሚለውን በተመለከተ ኢዜአ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል። 

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አደም ፈቶ፤ ስራ አጥነት፣ የዋጋ አለመረጋጋት፣ የብድር ጫና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።  

የውጭ ምንዛሬ ክምችት እጥረት የማክሮ ኢኮኖሚው ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት ኤክስፖርትን ማበረታታትና የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጮችን ማስፋት ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም አሁን ላይ ወርቅ የወጭ ንግዱን ለማሳደግ አማራጭ ምርት እንደሆነ ይናገራሉ።

የወርቅ ምርትን ለማበረታታት ብሄራዊ ባንክ ከአለም አቀፍ ገበያው 35 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ወርቅ መግዛት መጀመሩን አስታውሰው ይህም የውጭ ምንዛሪ ክምችትን በማሳደግ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። 

ባንኩ የጀመረው ማበረታቻ በባህላዊ መንገድና በአነስተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ወርቅ አምራቾች የበለጠ ምርታማ እንዲሆኑና አገር የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ያስችላል ያሉት ደግሞ የልማት ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ደረጄ ደጀኔ ናቸው።

ሆኖም ዘርፉ አሁንም በህገ ወጥ ግብይት እየተፈተነ ከመሆኑ ባለፈ የወርቅ አምራቾች ባህላዊ መንገድን ተከትለው የሚሰሩ በመሆናቸው የእውቀትና ቴክኖሎጂ እገዛን ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በወርቅ ምርት ላይ የተሰማሩ አካላትም ህገ-ወጥ ግብይትን ለመከላከል የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም