ቀጥታ፡

በሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተወያይተዋል

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥር 4/2015 በሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ማወያየቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረውን 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የተከናወነበትን ሂደት ዛሬ ገምግሟል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ኡመድ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ስኬታማ በሆነ መልኩ መከበሩን ገልጸው ሰፊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተከናወነበት መድረክ ነበር ብለዋል።

በበዓሉ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህልንና እሴታቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ በሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ለሀገር ብልጽግና ከመቼውም ግዜ በላይ ለመስራት ቃል የተግባቡበት ነበር ብለዋል።

የበዓሉን አገር አቀፍ አከባበር በተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የበይነ መንግሥታት ግንኙነት፣ የብዝኃነትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር ትግሉ መለሠ እንዳሉት በበዓሉ አከባበር ስለ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት ምንነትና አፈጻጸም ላይ ውይይት መደረጉን አንስተዋል።

በውይይት መድረኮቹ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የሚገኙ 7ሚሊዮን 289 ሺህ 609 ሰዎች በሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በማስመልክት የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና የችግኝ ተካላ የማህበራዊ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል ብለዋል።

በዲፕሎማሲው ዘርፍም የሩሲያ፣ ኩባ፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ቻይና ተወካዮች 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መታደማቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም