ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባኤርቦክ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪ ኮሎናን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹም ዛሬ ረፋድ ላይ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
የውይይታቸውም ትኩረት የአገሮቹን የረጅም ዘመን የዘለቀ ሁለተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ችግር ለመፍታት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሚደረገው መልሶ ግንባታ ሁለቱ አገራት ድጋፍ እንደሚያደርጉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል።
ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ በተለይም በድህረ-ስምምነት ተግባራት ሴቶችን አካታችና ተሳትፎ ታሳቢ ያደረጉ የመልሶ የማቋቋም ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ በውይይቱ ተነስቷል።
የፈረንሳይ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ጉብኝት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን
በቆይታቸው በሁለትዮሽና ሁሉን አቀፍ የትብብርና ዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከጀርመን እና ከፈረንሳይ ጋር ከአንድ ምዕተ ዓመት የተሻገረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።