የኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ወዳጅነትና ሁለንተናዊ ትብብር እየተጠናከረ ነው- አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ወዳጅነትና ሁለንተናዊ ትብብር እየተጠናከረ ነው- አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ወዳጅነትና ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለጹ።
ኢትዮጵያና ሱዳን በአፍሪካ ቀንድ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካና ማህበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ትስስር ያላቸው ወዳጅ አገሮች መሆናቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም ጠንካራ ትስስር ያላቸው ጎረቤት አገሮች ናቸው።
የአገሮቹን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የሁለቱ አገሮች የቆየ ወዳጅነት በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በሁለቱ አገሮች መካከል በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የትብብር ግንኙነት መኖሩንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ረዥም ድንበር የሚጋሩ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል የንግድና የልማት ትስስሩ እንዲሁም አብሮነቱን የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ተገናኝተው የሁለትዮሽ ምክክር ካደረጉ በኋላ የሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁለቱ አገሮች በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ መሆናቸውን አምባሳደር ይበልጣል አብራርተዋል።
በቀጣይም የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከኢትዮጵያ ባለፈ አጠቃላይ ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ መሆኑን አምባሳደር ይበልጣል ተናግረዋል።