ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ ክፍያ ውል መድሃኒቶችን ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ ክፍያ ውል መድሃኒቶችን ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ውል የተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት ትግበራ የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ከ28 ሆስፒታሎች ጋር አካሂዷል።

አገልግሎቱ ከሆስፒታሎቹ ጋር ውል የገባው ፍላጎትን መሠረት ባደረገ የአሰራር ስረአት ነው።

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከኮቪድ መከሰትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት በጤና ተቋማት የመድኃኒት እጥረት እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የአቅርቦት ሁኔታ በቅደመ-ክፍያ የአሰራር ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የተጀመረው የአሰራር ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚታየውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር 80 በመቶ የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በተለይ 150 የህይወት አድንና ሌሎች መድኃኒቶችን ለ28 ሆስፒታሎች በቅደመ-ክፍያ ውል ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል። 

በዚህም የአሰራር ሥርዓት ቢያንስ 95 በመቶ የአቅርቦት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ ግብ እንደተጣለ አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሙከራ ደረጃ ሲሰራበት የቆየው የፈጣን ለውጥ አምጪ ዕቅድ ሥርዓትን በሆስፒታሎች የሚጀመር መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና ፕሮግራም የሚሰጡ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ፣ ወባ እና የክትባት መድኃኒቶች በመሠረታዊ የመድኃኒት አሰራር ሥርዓቱ ላይ እንዲዘረጉ ይደረጋል ብለዋል። 

መድኃኒቶቹንም በየ 15 ቀኑ ለሆስፒታሎቹ እንደሚያቀርብም አስረድተዋል። 

በአጠቃላይ በአገልግሎቱ የተገዙ መድኃኒቶችን ዉል ለገቡ ሆስፒታሎች የማድረስ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም