በኢህአዴግ ጉባኤ አገራዊ አንድነትን የሚያመጡና ወጣቱን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እንጠብቃለን-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢህአዴግ ጉባኤ አገራዊ አንድነትን የሚያመጡና ወጣቱን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እንጠብቃለን-ነዋሪዎች
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አገራዊ አንድነትና ብሄራዊ መግባባትን የሚያመጡ እንዲሁም ወጣቱን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እምነታቸውን ገለጹ። በኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በየሁለት ዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመት ተኩል ድርጅታዊ ጉባኤው ይካሄዳል። የኢህአዴግ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ደግሞ ከመስከረም 23 እስከ 25 በሃዋሳ ከተማ ይካሄዳል። ጉባኤው "በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴን በማስቀጠል የአገራችንን ሕዳሴ እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይም የሚመክር ይሆናል። በዚህም "በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች አገራዊ አንድነትን የሚያመጡ፣ የህዝብን ጥያቄ የሚመልሱ እና ወጣቶችንም ያማከሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እንጠብቃለን" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አባይነህ ጥላሁን አገራዊ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ ወጣት መሳይ ካሳሁን በበኩሉ አዲስ የሚመጣው ሂደት አንደ አገር የሚያመጣው ለውጥ በጣም የተሻለ ነው ብዬ አስባለው ከውሳኔው በጣም ብዙ ነገር እጠብቃለሁ ብሏል፡፡ በቀጣይ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥ ህብረተሰቡ የለውጥ አካል በመሆን በኃላፊነት ስሜት ከመንግስት ጎን በመቆም በጋራ መስራት ይገባዋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ራሳቸውም ለአገሪቱ ሰላምና እድገት ዘብ ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በጉባኤው ድርጅቱ ባለፉት አምስት ወራት ባከናወናቸው ተግባራትና የተደረገውን የአመራር ለውጥ ተከትሎ የታዩ መልካም ጅምሮችን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሀሳቦችን ያካተተ ሰነድ በጉባኤው ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። በ10ኛው የድርጅቱ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና አፈፃፀምን በመገምገም እስከ 12ኛው ጉባኤ ድረስ የሚተኮርባቸው ዋና ዋና ሀሳቦች ላይ በስፋት ምክክር የሚደረግም ይሆናል። በጉባኤው በአጠቃላይ ከአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ድምፅ ከሚሰጡ ተሳታፊዎች በተጨማሪ ሌሎች የፌዴራል መስሪያ ቤትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃላፊዎች፣ የተለያዩ ማህበራትና ፌደሬሽኖችን ጨምሮ ከ1 ሺህ 900 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።