በያዝነው ዓመት የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ላይ በሰፊው ይሰራል- የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች መድኃኒት ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በያዝነው ዓመት የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ላይ በሰፊው ይሰራል- የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች መድኃኒት ጽህፈት ቤት
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 በያዝነው 2011 ዓመት አበረታች መድኃኒትና ቅመማ ቅመሞች ምርመራ ላይ በሰፊው እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች መድኃኒት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጽሕፈት ቤቱ ከተለያዩ የስፖርት ማህበራትና ከስፖርት ስልጠና ተቋማት በመጡ ባለሙያዎች፣ ሃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል። የጽሕፈት ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችና የምርመራ ስራዎችን በማከናወኑ ረገድ ውጤታማ ስራ እንደተሰራ ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት የአትሌቲክስ ስፖርትን ጨምሮ በእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ በብስክሌት ስፖርተኞች፣ በቦክስና የፓራ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ከ730 በላይ ስፖርተኞች ላይ የደምና የሽንት ናሙና መሰብሰቡን ነው የገለጹት። በጸረ አበረታች መድኃኒት ዙሪያ መድረኮች እየተዘጋጁ የሚመለከታቸውን አካላት የማወያየትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራም ተሰርቷል ብለዋል። እነዚህም የምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ውጤታማ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ይሁን እንጂ ጽህፈት ቤቱ ባለፉት ስራዎቹ ሳይዘናጋ በዚህ ዓመትም በርካታ የቤት ስራዎች እንደሚጠበቁበት ነው የገለጹት። በዚህ መሰረትም በያዘነው 2011 ዓ.ም ወደ 800 በሚጠጉ ስፖርተኞች ላይ የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ለማካሄድ መታቃዱን ነው የገለጹት። ከዚህ በተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ከዚህ በፊት ይደረግ ከነበረው በተለየ ጥልቀት ባለው መልኩ ለመስጠት እንደታሰበ ፕሮፌሰር አክሊሉ ተናግረዋል። እነዚህን ስራዎችን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወንም በጽህፈት ቤቱ ስር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል። በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊዎች በሀገሪቱ የሚታዩ የአበረታች መድኃኒትን መከላከል ስራ ውጤታማ ያደርጋል ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ አሁንም ቢሆን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስፖርተኞች አበረታች መድኃኒት ይጠቀማሉ በሚል ትኩረት ካደረገባቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን መገንዘብና መስራት ያስፈለጋል። ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና ማናጀሮችም የአበረታች መድኃኒትን በቸልታ ሊመለከቱት እንደማይገባ ተናገሯል። የቀድሞ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስፖርተኞች ተወዳዳሪ ሊሆኑ በሚችሉባቸው መልኩ በቂ ዝግጅት ካደረጉ ወደ እነዚህ አይነት ያልተገቡ ስራዎች እንደማይገቡ ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመፍታት አንዱ መፍትሄም ልምምዱን በአግባቡ መስራት መሆኑ በመገንዘብ ማንም ስፖርተኛ ስልጠናው ላይ ትኩረት አድረጎ መስራት ይገባል ሲሉም ተናገረዋል። ባለፈው የ2009 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ አበረታች መድኃኒት ተጠቅመው በመገኘታቸው ስድስት አትሌቶች ቅጣት ሲተላለፍባቸው አምስት አትሌቶች ደግሞ ጉዳያቸው እየታየ ያለ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።