ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥር 3/2015 ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን ገለጹ።
በአዲስ አበባ የተገነባው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲ ዲ ሲ) የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን እና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማኅማት ማዕከሉን መርቀውታል።
በቻይና መንግሥት የገንዘብና የምህንድስና ሙያ ድጋፍ የተገነባው ማዕከል ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታው እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል።
ከምርቃት መርሐግብሩ በኋላ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን በሰጡት መግለጫ፤ ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጠንካራና ተመጋጋቢ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አላት ብለዋል።
በተለይም በምጣኔ ሀብት የትብብር መስኮች ላይ ያላቸው ግንኙነት ፍሬያማ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን የጋራ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ዕድሎችን ታፈላልጋለች ነው ያሉት።
በተለይም ደግሞ ቻይና ከአፍሪካ የልማት ፍላጎት ጋር ያላትን ቁርኝት በማጠናከር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ለማፋጠን ትሰራለች ብለዋል።
በቻይናና በአፍሪካ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሚያስችሉ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለማጠናከርም እንደሚሰራም አክለዋል።
አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተና የሆኑት የአየር ንብረት ለውጥ፣ ወረርሽኝና ሌሎች ተግዳሮቶችን በጋራ ለመመከትና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀትም ቻይና አጋርነቷን ታጠናክራለች ብለዋል።
የዓለም የፖለቲካ ስርዓት ፍትሃዊና ሁሉን አሳታፊ ለማድረግ አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫና እንዲሁም በቡድን 20 አገራት አባል እንድትሆን ቻይና ድጋፏን እንደምታጠናክር ገልጸዋል።
ቻይና "ባዶ ቃል አትገባም " ያሉት ቺን ጋን አፍሪካ ጠንካራ አህጉር እንድትሆን የሰነቀቻቸውን ግቦችን ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበኩላቸው፤ ቻይና ለአፍሪካ አገራትና ለአፍሪካ ሕብረት ተጨባጭ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው፤ ይህም ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ አገራት ወደብ፣ መንገድ፣አየር ማረፊያ፣ባቡርና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን በመገንባት አፍሪካ ራሷን የቻለች ጠንካራ አህጉር እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች ብለዋል።
በፖለቲካው መስክም በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
ቻይና በአፍሪካ አገራት ለምታደርጋቸው ድጋፎች አመስግነው፤ በቀጣይ ቻይና ከአፍሪካ ኅብረትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።