በዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የወከሉት ክለቦች ዳግም ተሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የወከሉት ክለቦች ዳግም ተሸነፉ
አዲስ አበባ መስከረም 222011 የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የወከሉት ክለቦች በሁለተኛ ጨዋታቸውም ሽንፈትን አስተናገዱ። ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች የተካፈለችበት የዞን አምስት የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና በታንዛኒያ ዳሬሰላም እየተካሄደ ነው። ውድድሩ በወንዶች ለ33ኛ ጊዜ በሴቶች ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል። በወንዶች ወልቂጤ እና ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች፤ በሴቶች ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ኢትዮጵያን ወክለው እየተካፈሉ ይገኛል። ከትናንት በስቲያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሶስቱም ክለቦች ሽንፈትን እንዳስተናገዱ ይታወቃል። በትናትናው እለትም የምድብቸውን ሁለተኛ ጨዋታ ያደረጉት ወልቂጤ ከተማና የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች በሰፊ ጎል ልዩነት ተሸንፈዋል። ወልቂጤ ከተማ ከግብጹ አልሃሊ ጋር ባካሄደው ጨዋታ 36 ለ 113 በሆነ ቅርጫት ሽንፈትን አስተናግዷል። በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች በኬኒያ ኬፐኤ ክለብ 85 ለ 50 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። በዛሬው እለትም ወልቂጤ ከተማ የብሩንዲውን ኒው ስታር፤ ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ደግሞ የታንዛኒያውን ጄኬቲ ክለብ ይገጥማሉ።