ኢትዮጵያ የሥጋ ምርቷን ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ልትልክ ነው - ግብርና ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሥጋ ምርቷን ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ልትልክ ነው - ግብርና ባለሥልጣን
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ጥር 3/2015 ኢትዮጵያ የሥጋ ምርቷን ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ገበያዎች ለመላክ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ የኤክስፖርት ቄራ ቁጥጥርና ፈቃድ ዳይሬክተር ዶክተር አያሌው ሹመት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓመት ከ200 ሺህ ቶን በላይ የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ቢኖራትም አሁናዊ አቅርቦቷ ግን ከ22 ሺህ ቶን አይበልጥም።
በዚህም የሥጋ ምርት መዳረሻ ከሆኑ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በተጨማሪ ወደ ሩቅ ምስራቅ ገበያ ለማስፋት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ከሦስት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ላይ በተሰሩ ሥራዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ በተጨማሪ ወደ ቬትናም እና ኮሞሮስ የሥጋ ምርቷን ማቅረብ መጀመሯን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት ምርቱን በቋሚነት ከምትልክባቸው የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያና ኳታር በተጨማሪ ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ ገበያ ለመግባት ቅድመ-ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ወደ ገበያው ለመግባትም ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ባሻገር በሥጋ ምርት አቅርቦት ዙሪያ ላይ የተለያዩ ጥናቶች እየተከናወኑ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በባለሥልጣኑ የእንስሳት ምርት ጥራትና ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር በላቸው ባጫ በበኩላቸው፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የሥጋ ምርት ጥራቱን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ይላሉ።
በዚህም የላቦራቶሪ ምርመራ ሥራዎችን በማጠናከር የምርት ጥራቱን፣ ደኅንነቱን የማስጠበቅ እና የሥጋ ምርትን ለመጨመር አየተሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
ወደ ቻይና እና ኢንዶኔዥያ የሚላኩ የሥጋ ምርቶችንም አገራቱ በሚፈልጉት መንገድ ፍተሻዎች እየተደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ላቦራቶሪው በአሁኑ ወቅት ከሚገኙ የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪዎች ተርታ በሚመደብ መልኩ የተደራጀ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር በላቸው፤ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተያዘው ግማሽ በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋ ምርት 50 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ የሥጋ ምርት በጥራት ተመራጭ ቢሆንም በሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ፣ ከእርባታ እስከ ኤክስፖርት ባሉ የእሴት ሰንሰለት ችግሮች ሳቢያ በሚፈለገው ደረጃ እንዳላደገ ዶክተር አያሌው ገልጸዋል።
በዚህም ተግዳሮቶቹን በማስተካከል የወጪ ምርት መጠኑን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በታሪክ ከፍተኛ የተባለ 22 ሺህ ቶን በላይ የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቦ 119 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 28 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለመላክ መታቀዱን ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት 7 ሺህ 200 ቶን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 50 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው ግኝት ግን በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ሳቢያ ካባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ2 ሺህ 800 ቶን ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።