የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 70 በመቶ የሚሆነው ወጪ የሚውለው ለተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 70 በመቶ የሚሆነው ወጪ የሚውለው ለተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 3/2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 70 በመቶ የሚሆነው ወጪ የሚውለው ለተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ፡፡
በጥናቱ በፕሪሚየር ሊጉ የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ክፍያ በአማካይ ከ130 ሺህ ብር በላይ መድረሱ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ‘ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና የልማት ፍኖተ ካርታ' በሚል ርዕስ ያስጠናው ፁሑፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይት እየተደረበት ነው።
በታውንሰንድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት የጥናቱ አቅራቢ ዶክተር ጋሻው አብዛ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንድ ተጫዋች አማካይ የደሞዝ ክፍያ ከ130 ሺህ ብር በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
የተጫዋቾች ወርሃዊ አማካይ ክፍያ ኢትዮጵያን በአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፍሉ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት እንደሆነ ገልጸዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት ለተጨዋቾች ደሞዝ ብቻ በአማካይ 40 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መሆኑ ታውቋል።
ይህ ማለት ደግሞ ክለቦች 70 በመቶ የሚሆነው ወጪያቸው ለተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ የሚያውሉ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
የሊግ ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ መቶአለቃ ፍቃደ ማሞ አክሲዮን ማህበሩ ከተመሰረተ ሶስተኛ ዓመቱን መያዙን አስታውሰው በዚሁ ጊዜ ሊጉን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ከፌደሬሽን ወጥተው በሊግ አክሲዮን ማህበር መመራት ከጀመሩ በኋላ ገቢ ማመንጨት መቻላቸው እንደ ጅምር አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እግር ኳሱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያ ማድረግ በማስፈለጉ ጥናቱ መከናወኑን አስታውሰዋል።
የጥናት ግኝቱን ባለ ድርሻ አካላት ተግባራዊ ካደረጉት እግር ኳሱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ለእግር ኳስ ልማት ስራው ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በማስታወስ ክለቦቹ ጥናቱን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የገንዘብ አቅማቸውን በማጠናከር ከተረጅነት ይወጣሉ ብለዋል፡፡
ይህም ቡድኖቹ ራሳቸውን የሚችሉበትን እድል እንደሚፈጥርላቸው በመግለጽ በሂደት ከሀገር ውስጥ አልፈው በሌሎች ሀገራት ሊጎች የሚጫወቱ ብዛት ያላቸው ተጫዋቾች ለማፍራት እንደሚረዳቸው አንስተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በእግር ኳስ ውድድሮች የሚመዘገቡ ውጤቶች ህዝባዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ጥናቶች እግር ኳሱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ በመሆናቸው ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል ።
መንግስት እግር ኳሱን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶችን ውጤታማ ለማድረግ የአደረጃጀት ማሻሻያ ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል ።