ቀጥታ፡

በውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የባህል ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚሰጥ ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 3/2015 በውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የባህል ዲፕሎማሲ ትኩረት እንደሚሰጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ለሚሲዮን መሪዎች "የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በተለወጠው የዓለም አሰላለፍ" በሚል ርዕስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የባህልና የስፖርት ዲፕሎማሲ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ቁልፍ አገራዊ ተቋሞችን ለስኬታማ የስራ ስምሪት አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓለማቀፋዊ ፈተናዎችን እንዲሻገር ከውስጣዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ጎረቤት አገራት ላይ በማተኮር እና ለቀጠናው እና ለፓን አፍሪካ እሳቤ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በሁለትዮሽ እና በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ስራ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አቶ ደመቀ አስረድተዋል።

የዲፕሎማሲ ስራን በተመሳሳይ መንገድ በመስራት የተለየ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲፕሎማቶች ሙያዊ ክህሎታቸውን በየወቅቱ በማሳደግ ፈተናዎችን በብቃት እና በፅናት ለመሻገር ሁሌም ቀድመው መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የባለብዙ ወገን መድረኮችን በብቃት በመጠቀም የተጠናከረ ስራ እንደምትሰራም ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነትን የፈተኑ ሁኔታዎችን በሚመለከትም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዲፕሎማቶች በሁነቶቹ ውስጥ የሚፈጠሩ የአገራትን አካሄድና ፍላጎት በንቃት ተገንዝበው ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሆኑ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው ተናገረዋል።

የዲፕሎማሲ ድልን በመንግስት ተቋም ብቻ ማሳካት እንደማይቻል፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚገባ፣ ወቅታዊውን የዓለም ሁኔታ በምሳሌነት በመጥቀስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ አድርገዋል።

በቀጣይ በሁሉም ሚሲዮኖች የተቀናጀ የዲጂታል እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ መሰራት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም