በኢትዮጵያ ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ በሽታዎችን ለመከላከል የባለሙያና የአቅም ውስንነት አለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ በሽታዎችን ለመከላከል የባለሙያና የአቅም ውስንነት አለ
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 በኢትዮጵያ ለዓይነ ስውርነት ለሚዳርጉ በሽታዎች የሚጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ የባለሙያና የአቅም ውስንነት መኖሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አመልክቷል። ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የዘርፉን ባለሙያዎች አቅምና ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የአይን ህክምና ስልጠና በመስጠትና ህክምና በማድረግ የሚታወቀው ኦርቢስ ኢንተርናሽናል በአዲስ አበባ ለሦስት ሳምንት የሚሰጠውን አገልግሎት ዛሬ ጀምሯል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት እይታቸውን እያጡ ያሉ ዜጎች ቀላል የማይባል ሲሆን እንደ አገር ያለው የዘርፉ ባለሙያ በቁጥርም ሆነ በአቅም ውስንነት ያለበት ነው። ኦርቢስ ኢንተርናሽናል እስካሁን ድረስ በ110 አገሮች እየተዘዋወረ የሰራ ሲሆን ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑንና ችግሩን ለማቃለል የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ትልቅ ሚና መወጣቱንም ገልፀዋል። ሚኒስቴሩ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያትና በሞራ ግርዶሽ የሚመጣ አይነ ስውርነትን ለመቀነስ የዘርፉን ዶክተሮች በቁጥርና በክህሎት ለማሳደግ ከዩኒቨርስቲዎችና ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጀመሩ ደግሞ የተያዘውን ጥረት ከዳር ለማድረስ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አሁን ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን ላለፉት ሃያ አመታት ከአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ ሃዋሳና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የክህሎት ማስተላለፍ ስራ አስተዋፅኦ አድርጓል። በኦርቢስ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ሲሳይ በበኩላቸው ድርጅቱ ላለፉት ሃያ አመታት ለዘርፉ ባለሙያዎች የእውቀት ሽግግር በማድረግ በአገር ውስጥ ህክምና የሌላቸውን የአይን ህመሞች ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል ''ለአብነትም የህፃናት የአይን ህክምና፣ የአይን ባንክ፣ የአይን ጠባሳ ህክምና የአይን ግፊት ወይም ግላኮማ ህክምና የሚጠቀሱ ናቸው'' ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከ100 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ማጥናቱንና ለሆስፒታሎችና ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ለሚመለከታቸው አካላት ግብአትነት እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል። በቀጣይም እንደ ትራኮማና ተያያዥ የአይን በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን የአይን በሽታዎች ለማከም እንዲቻል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥም እስከ 355 ባለሙያዎችን ልዩ የአይን ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግና ከ250 በላይ ህመምተኞችን ለማከም አቅዶ በኢትዮጵያ አየር ማረፊያ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአይን በሽታ ዶክተሮች ቁጥር 140 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና የሚሰጡት 56ቱ ብቻ ናቸው። ለዚህም አገሪቱ አሁን በዘርፉ የጀመረችውን የድህረ ምረቃ አገልግሎት ወደ ስፔሻላይዜሽን የማስገባት ስራ እየሰራች መሆኑንና የአቅምና የተደራሽነት ማስፋት ስራ እየተሰራ ይገኛል።