የፌዴሬሽን ምክር ቤት በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ባለቤትነት ጥያቄ ለመመለስ የቀረበውን ሃሳብ ለጋራ ምክር ቤት መራ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ባለቤትነት ጥያቄ ለመመለስ የቀረበውን ሃሳብ ለጋራ ምክር ቤት መራ
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥር 3/2015 የፌዴሬሽን ምክር ቤት በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ የባለቤትነት ጥያቄ ለመመለስ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ለጋራ ምክር ቤት መራ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ከድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ባለቤትነት ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ መርቷል።
ውሳኔው በንብረት ላይ የሚጣል ታክስ ከተሞች ከንብረት የሚገኘውን ገቢ በሚገባ በመሰብሰብ የመሰረተ- ልማት አቅርቦትን ለማሻሻል በአግባቡ እንዲውል እንደሚያደርግ በውሳኔ ሃሳቡ ተመላክቷል።
ሁለቱ ምክር ቤቶች ዛሬ በሚያካሂዱት 1ኛ የጋራ ልዩ ስብሰባ የውሳኔ ሃሳቡን መርምረው ያጸድቁታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሚደረገው የጋራ ስብሰባ ከንብረት ታክስ የሚገኘውን ገቢ የመሰብሰብ ሥልጣንን ይወስናል ተብሎም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው በሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ-መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ በተሰጠባቸውና ለምክር ቤቱ በይግባኝ በቀረቡ 18 አቤቱታዎች ላይ ከሕገ-መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።