ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የሚመጥን የፖሊስ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው- የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ጥር 2 / 2015፡- ኢትዮጵያን የሚመጥን የፖሊስ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

በጅግጅጋ  በሚገኘው ገርባ አሴ የፖሊስ ማሰልጠኛ የሰለጠኑ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ባደረጉት ንግግር፤  የፌዴራል ፖሊስ   በእኩልነት ህዝቡን ለማገልገል በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሞክሩ የነበሩ ኃይሎችን ለመከላከል በተደረገው ትግል የፖሊስ አባላትና አመራሮች ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ትልቅ ዋጋ መክፈላቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ በተለያየ መልኩ ጫና የሚፈጥሩ ጠላቶች ቢኖርባትም በፀጥታ ኃይሎች ጥንካሬ እየተጠበቀች ትገኛለች ብለዋል።

አሁን ሰላም እየተረጋገጠ በመምጣቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አቅሙ ፊቱን ወደ ልማት ማዞሩን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ አክለውም ፖሊስ ይህን የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል  አረጋግጠዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ተቋም በአፍሪካ ደረጀ በማብቃት ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን  አድርጎ  ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ  መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን የበለጠ በማጠናከር ዘመናዊና ህግና ሥርዓትን አውቆ ህዝቡን የሚያገለግል የፖሊስ አባላትን ያፈራል ብለዋል።

የፖሊስ ኃይል የማሰልጠን ስራ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገልጸው፤ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሶማሌ ክልልም የክልሉ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ባደረገው የፀጥታ ማሰከበር ስራ ክልሉ ሰላማዊ መሆን ችሏል ብለዋል።

ከዕለቱ ተመራቂ የፖሊስ አባላትም በሀገሪቱ   የህግ በላይነት ለማስከበር እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት  ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ፖሊሳዊነት ህዝባዊነት መሆኑን በመረዳት ተመራቂዎች በዚህ መርህ በሕዝባቸው ፊት እንዲቆሙም አሳስበዋል።

ከኃይማኖት እና ከጎሰኝንት በፀዳ መልኩ መስራት ከተመራቂዎች ይጠበቃል ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ፤ ፖሊስ ህዝባዊነት ነው፤ ለሰው ልጅ እኩልነት መቆም ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ከሁሉም በላይ ፖሊሳዊነት ህዝባዊነት መሆኑን በመረዳት ተመራቂዎች በዚህ መርህ ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው የዕለቱ ተመራቂዎች የወሰዱት ስልጠና የሀገሪቱን  ሰላምና አንድነት በበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር  ሙስጠፌ አያይዘውም በክልሉ የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ሥራ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ፖሊስ ዋና ተግባሩ የህዝብ ሰላም ማስከበር በመሆኑ የዕለቱ ተመራቂዎችም ፖሊሳዊ ባህርይ ተላብሰው ህዝቡን በእኩልነት እንደሚያገለግሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ በስልጠና ቆይታቸው የቀሰሙትን ትምህርት ስራ ላይ በማዋል ለህግ የበላይነት መከበር ኃላፊነታቸውን አደራ በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንዲወጡ አቶ ሙስጠፌ አሳስበዋል።

 ራሳቸውን በመልካም ስነ ምግባር በማነፅ  በሙያቸው ከጎሰኝነት፤ ከአድሎ ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ አስታውቀዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ ህገ መንግሥቱንና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስከበር ከመንግሥትና ከህዝብ የተቀበሉትን አደራ በብቃት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም