ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማጠናከር ለዲያስፖራው ይበልጥ ተደራሽ መሆን አለበት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማጠናከር ለዲያስፖራው ይበልጥ ተደራሽ መሆን እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አሳሰበ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ድንገተኛ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማሕዲ የመስክ ምልከታው ዋነኛ ዓላማ  ተቋሙ ለምክር ቤቱ ያቀረበው ሪፖርትና በተግባር ያለው እንቅስቃሴ የተናበበ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡

በዚህም ተቋሙ በሪፖርት ካቀረበው አፈጻጸም ጋር የተናበበ ስራ እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እና ጣሊያን የመጡ ተገልጋዮችን በማናገር ተቋሙ ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን መገንዘባቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ተቋሙ የተሻለ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ አገልግሎት አሰጣጡን አሁን ካለበት ይበልጥ ማዘመን አለበት ብለዋል፡፡

በተለይ የጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ በማጠናከር ለዲያስፖራው ይበልጥ ተደራሽ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው፣ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ የዲያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል ለማድረግ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም