ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ እና የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄነራል አህመድ ሞአሊን ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
በስምምነት ፊርማ መርሃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ እና የሶማሊያ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ፈርዶውሳ ኦስማን ተገኝተዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ አገራት በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ሁለቱ አገራት በዘርፉ ያላቸውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ስምምነቱ "ያልተገደበ የበረራ ድግግሞሽ፣ አምስተኛ ደረጃ የተሳፋሪ ነፃነት እንዲሁም ሰባተኛ ደረጃ የጭነት ማጓጓዝ ነጻነት" የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪ ስምምነቱ የአህጉሪቱን አጀንዳ 2063 ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
በመሆኑም መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት በትኩረት እንደሚሰራም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
የሶማሊያ የትራንስፖርትና ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ፋርዶውሳ ኦስማን በበኩላቸው ስምምነቱ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት የካበተ ልምድ ተሞክሮ እንድንወስድ ያግዘናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ያልተገደበ የበረራ መዳረሻ እንዳላት የገለጹት ሚንስትሯ ስምምነቱ ይህን ይበልጥ የሚያጠናክር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ስምምነቱ በሁለቱ አገራት በዘርፉ የነበራቸውን ለ34 ዓመታት የቆየ ስምምነት በአዲስ ምዕራፍ የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ስምምነት መዳረሻ ቦታዎችን ይገድብ እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ስምምነት የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች በአገራቱ ባሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ያለገደብ ማረፍ እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ከሁለቱ አገራት ውጭ የሚሄዱ መንገደኞች እና እቃዎችን ማጓጓዝ የሚያስችል ስምምነት መሆኑንም ጠቁመዋል።