የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ባለፉት ስድስት ወራት ለኢንተርፕራይዞች የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብድር አሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ባለፉት ስድስት ወራት ለኢንተርፕራይዞች የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብድር አሰራጨ
አዳማ ኢዜአ ጥር 02/2015 ባለፉት ስድስት ወራት የኢንተርፕራይዞች አምራችነትን አቅም ለማጠናከር የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብድር እንደተሰራጨ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የኢንተርፕራይዞች የስራ ሃላፊዎች ጋር የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የስራ አፈፃፀም በአዳማ እየገመገመ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት 1ሺህ 647 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ከ13ሺህ 774 በላይ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል ብለዋል።
በዚህም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የማምረት አቅም እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር መደረጉንም ተናግረዋል።
ከስራ እድል ፈጠራ ባለፈ ከውጭ የሚገቡ ተኪ ምርቶችንና ወደ ውጪ የሚላኩ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ ያላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢንተርፕራይዞችን የካፒታልና ፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የኢንተርፕራይዞች የአምራችነት አቅም ለማጠናከር ለስራ ማስኬጃ የሚውል የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብድር እንደተሰራጨ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ለሊዝ ማሽን ግዥ የፋይናንስ አገልግሎት የሚውል 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር እንዲቀርብ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ያቆሙ 172 የሚሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስና የአቅርቦት ድጋፍ ተደርጎላቸው ዳግም ስራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በተሰናዳው የግምገማ መድረክ የዘርፉ ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ የሚካሄድ ሲሆን የየክልሎችም የስራ አፈጻጸም ተሞክሮ ቀርቦ ልምድ እንደሚለዋወጡበት ይደረጋል።