ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፕሬስ ህግ በአግባቡ ባለመተግበሩ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ስር እየወደቀ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 በኢትዮጵያ የፕሬስና የመገናኛ ብዙሃን ህግ በአግባቡ ተግባራዊ ሊደረግ ባለመቻሉ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ አድርጎታል ተባለ። ይህ የተባለው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አለም አቀፉን የመረጃ ነጻነት ቀን አስመልክቶ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው። በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት፣ የወጡ ህጎች አተገባበርና ክፍተቶቻቸው እንዲሁም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች በፓናል ውይይቱ ላይ ቀርበዋል። "በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የፕሬስ ህግ አፈጻጸም" በሚል መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የፕሬስ ሪፎርም ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ በአለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ነጻነት ህግ ሊይዛቸው የሚገቡ ነጥቦችና የኢትዮጵያ ህግ በይዘት ደረጃ ተመሳሳይ እንደሆኑ ጠቁመዋል። ህጉ የተሻለ ይዘት ቢኖረውም በተግባር ጥቅም ላይ ለማዋል የማስፈጸሚያ መንገዶች ላይ ክፍተት በመኖሩ ህግ ማውጣትና ለህጉ ተፈጻሚነት አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ለመብቱ ተፈጻሚነት የሚመለከታቸው አካላት የተቀናጀ ጥረትም ወሳኝ መሆኑን  አብራርተዋል። መረጃን ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ፍጥነቱን ወይንም ተግባራዊነቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ስነ ስርአቶችን መደንገግ አስፈላጊ እንደሆነ የወጡ ድንጋጌዎች ያሳያሉ። በዚህ በኩል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአፈጻጸም ላይ ክፍተት እንዳለ ነው የሚያስቀምጡት። ኢትዮጵያ ክልከላ ያደረገችባቸው መረጃዎችን በተመለከተ ውስን ባይሆኑም የሰጠቻቸው የክልከላ ምክንያቶች "በሌላው አለም ያልተለመዱና" በርካታ ናቸውም ይላሉ። በአጠቃላይ የወጡ ህጎች ችግር ባይኖርባቸውም አፈጻጸማቸው ላይ ክፍተት በመኖሩ ዜጎች መረጃን ለማግኘት ሌሎች አማራጮችን እንዲያዩ እያደረገ ነው። እኤአ በ2011 በወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 1 በመቶ ህዝብ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ነው። የፓናል ውይይት መድረኩ ተሳታፊ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ማህበራዊ ሚዲያን አስመልክቶ ባቀረበው ሃሳብ "ዋናው ሚዲያ በመረጃ ነጻነት ላይ በትክክል አለመስራቱ እውነትንና እውቀትን ማጣጣም ያልቻለ የማህበራዊ ሚዲያ እንዲፈጠር አድርጓል።" "በማህበራዊ ሚዲያው ተጽእኖ ስር እንድንወድቅ ያደረገን ዋናው መስመር አለመስራቱ ነው" የሚል እምነትም አለው። በኢትዮጵያ ከሚገኘው 1 ነጥብ 1 በመቶ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ውስጥ 93 በመቶ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ 25 እስከ 30 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን ያነሳል። ዋናው ሚዲያ በመረጃ እጥረት፣ በአቅም ክፍተት፣ መረጃን በወቅቱ ባለማግኘቱ የተነሳ ማህበራዊ ሚዲያው የሰዎችን ቀልብ የሳበበት ምክንያት መፈጠሩን ያስረዳል። ዋናው ሚዲያ መረጃን በፍጥነት አለማግኘትና የታማኝነት ችግር ገጥሞታል ሲልም ይጨምራል። በመገናኛ ብዙሃንና በጋዜጠኞች ላይ የተጣለው የህግ ተጠያቂነት እየጠበቀ መምጣት ብዙ ባለሙያዎች ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። እንደ ዲያቆን ዳንኤል ገለጻ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ ባለማግኘታቸው ከእውነት ይልቅ አመለካከት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በዋናው ሚዲያ በኩል በትክክል ባለመሰራቱ የማህበራዊ ሚዲያውን ሚና የጎላ በማድረግ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ስር እንዲወድቅ ማድረጉን ተናግሯል። ማህበራዊ ሚዲያው በእውቀትና በመረጃ ባለመመራቱ የግለሰብን ስም የማጥፋት፣ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትና ሌሎች ቀውሶች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው። መረጃ ካለመስጠት ጋር በተገናኘም በተቋማት ውስጥ ያሉ ድብቅ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ማን እንዳወጣቸው ሳይታወቁ እንደሚለጠፉ በመግለጽ መረጃ አለመስጠት መረጃውን ይፋ ከመሆን እንደማያድነው አስረድቷል። በፈጣን እድገት ላይ ካለው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብሮ የሚሄድ የመረጃ ህግ እስካልተፈጠረ ድረስ በቀጣይም ማህበራዊ ሚዲያው ዋናውን ሚዲያ መምራቱ እንደማይቀር ገልጿል። የህግ ባለሙያው አቶ ይርሳው ዘውዴ የማስፈጸሚያ ህግ አለመኖር የመረጃ ነጻነት ህጉ በሚፈለገው መንገድ እንዳይተገበር ማድረጉን ተናግረዋል። በቀጣይ በሚዘጋጀው የፕሬስ ሪፎርም ላይ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃና የፈጻሚውን አካል ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችል ሃሳብ ማካተት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙ የተለያዩ ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች መረጃ ከመስጠት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንዳሉ አንስተዋል። ችግሩ በተቋሙ ሃላፊዎችና በህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ላይም እንደሚስተዋል በማንሳት በአብዛኛው የሚታየው በሃላፊዎች ደረጃ መሆኑን ገልጸው ከአመለካከትና ክህሎት ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት መንስዔ እንደሆነ አመልክተዋል። በተጨማሪም በግልና በህዝብ ሚዲያዎች በኩል ያለው የመረጃ አጠያየቅና አዘጋገብ ሁኔታ ሃላፊዎች መረጃ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ያደረጋቸው መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም