ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ሰላምና ልማት ሥራዎች ዳያስፖራው የላቀ አበርክቶ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ሰላምና ልማት ሥራዎች ዳያስፖራው የላቀ አበርክቶ አድርጓል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ፣ ሰላምና ልማት ሥራ ዳያስፖራዎች የላቀ አበርክቶ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከአጋር ድርጅት ጋር በመሆን "ኢትዮ-ዳያስፖራ አዋርድ" በሚል መሪ ሃሳብ በተያዘው ወር የሚያካሄደውን የዕውቅና መርሃ-ግብር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
መርሃ-ግብሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከአይ ኤስ ፕሮሞሽንና ስፔሻል ኤቨንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በጋራ በመሆን መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ፤ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በያሉበት ሀገራት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ሚናቸውን መወጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በመሻገር ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ባደረገችው ጥረት በዕውቀትና ሀብታቸው ጭምር ትልቅ አበረክቶ አድርገዋል ብለዋል።
አገልግሎቱ ለዳያስፖራ አደረጃጀቶቹ ምስጋና ለመስጠትና ለበለጠ ሥራ ለማነሳሳት ያለመ የዕውቅና መርሃ- ግብር ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ከ25 የውጭ ሀገራት የተውጣጡ 45 የተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ዕውቅና የሚሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይ የዳያስፖራ አደረጃጀቶቹ በጋራ አንድ ጥምረት ፈጥረው ለሀገራቸው ሁለንተናዊ እድገት የሚሰሩበት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጠር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የአይ ኤስ ፕሮሞሽን እና ስፔሻል ኤቨንትስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢድሪስ ቦንሱሩ በበኩላቸው፤ በዕውቅና መርሃ-ግብሩ በውጭ የሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ያከናወኑትን ተግባር የሚዳስስ መጽሐፍ እንደሚመረቅ ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ የዳያስፖራ አባላትን እውቅና መስጠትና ማመስገን ለላቀ ሥራ የሚያዘጋጅ መሆኑንም ገልጸዋል።