ከውጭ በሚገቡ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ አስገዳጅ የደረጃዎች ቁጥጥር ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከውጭ በሚገቡ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ አስገዳጅ የደረጃዎች ቁጥጥር ተግባራዊ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ አስገዳጅ የደረጃዎች ቁጥጥር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢንስቲትዩቱ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር ይልማ መንግሥቱ፤ የምርት ጥራትና ደረጃን በማስጠበቅ ሂደት የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ የጥራትና ደረጃ ቁጥጥር ጉዳይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከውጭ በሚገቡ አንዳንድ የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ አስገዳጅ የደረጃ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
አንዳንድ አስመጪዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከተቀመጠው ደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ሲያስገቡ መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ቁጥጥሩን አጠናክሯል ብለዋል።
ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ደረጃዎችን በማዘጋጀት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲገባ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዝቅተኛ የጥራት መስፈርት በማያሟሉ አስመጪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ ዝግጅት በሂደት ላይ መሆኑንም አቶ ይልማ ገልጸዋል።
የጥራት ደረጃ የማያሟሉ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ተጨማሪ ኪሳራ ከማድረሳቸው በፊት ከሚነሱበት አገር የጥራት ማረጋገጫ ይዘው እንዲመጡ የሚያስችሉ አሰራሮች መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ በርካታ ምርቶችን የምታስገባ እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም በአንዴ አስገዳጅ ማድረግ ባይቻልም የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የምርት ጥራት ጉዳይ የአንድ አገር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና የዕድገት መሰረት በመሆኑ በኢንስቲትዩቱ በኩል በተለየ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።