ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ልማትና የገጽታ ግንባታ ስራ ላይ የላቀ ተሳትፎ ያደረጉ ዳያስፖራዎች እውቅና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 2/2015 በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና የገጽታ ግንባታ ስራ ላይ የላቀ ተሳትፎ ያደረጉ ዳያስፖራዎች የእውቅና መርሃ ግብር ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

የእውቅና መርሃ ግብሩን በማስመልከት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ እንዲሁም የገፅታ ግንባታ ስራ ላይ ከፍተኛ  አስተዋጽኦ ላደረጉ የዳያስፖራ አባላት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም የእውቅና መርሃ ግብር ይካሄዳል ብለዋል።

በገንዘብ እና በእውቀት ጭምር ለአገራቸውና ህዝባቸው የላቀ ተሳትፎ በማድረግ የሚጠቀሱ ዳያስፖራዎችም እውቅና ይሰጣቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም ከ25 የተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እውቅና የሚሰጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ ዳያስፖራዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም